የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ጥራትና ደረጃ ፍተሻና ቁጥጥር እያከናወነ መሆኑን የኦሮሚያ የግብርና ግብዓት ቁጥጥር ባለስልጣን ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ጥራትና ደረጃ ፍተሻና ቁጥጥር እያከናወነ መሆኑን የኦሮሚያ የግብርና ግብዓት ቁጥጥር ባለስልጣን ገለፀ

አዳማ ፣የካቲት 19/2016 (ኢዜአ) ፦የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓት ጥራትና ደረጃቸውን ጠብቀው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆኑ የቤተ ሙከራ ፍተሻና የቁጥጥር ስራ እያከናወነ መሆኑን የኦሮሚያ የግብርና ግብዓት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ሃላፊ አቶ አህመድ ሰዒድ ለኢዜአ እንደገለጹት የምርጥ ዘርና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ጥራት ለማስጠበቅ የምርጥ ዘር ድርጅትን ጨምሮ ከ96 አምራቾች ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርጥ ዘር በሚያባዙ የመንግስት ማዕከላት፣ በአምራች ድርጅቶችና በባለሃብቶች ከማሳ ጀምረው በሚከናውኑት የብዜትና አመራረት ሂደት ላይ የቁጥጥርና ክትትል ስራ እያከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዘንድሮው የምርት ዘመን በቤተ ሙከራ ፍተሻ የተረጋገጠና በቁጥጥር ስርዓቱ ውስጥ ያለፈ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል የተለያዩ ሰብሎች ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ አቅደው እየሰሩ መሆኑን በማከል።
በአሁኑ ወቅት ለበልግና ለአገዳ ሰብል አብቃይ አካባቢዎች የሚሆን በቆሎና ሌሎች ምርጥ ዘር የፍተሻና ቁጥጥር ስራው ተጠናቆ ጥራቱን የጠበቀ ዘር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም እንደ አብነት አንስተዋል።
በተመሳሳይ ከውጭ የሚገቡ የአፈር ማዳበሪያና ፀረ አረም ኬሚካሎች ጥራታቸውን የጠበቁና የተመዘገቡ መሆናቸውን የመፈተሽ ስራ እያከናወኑ መሆኑን የገለጹት አቶ አህመድ፤ በዚህም በክልሉ በሚገኙ ስድስት ቤተ ሙከራዎች የፍተሻና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
ምርጥ ዘር ከማምረት ጀምሮ በአሰባሰብ ሂደትና በማከማቻ መጋዝኖች አመችነትና ጥራት ላይ አርሶ አደሩ እጅ ደርሶ ውጤታማነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ የክትትል ስራው ይከናወናል ብለዋል።
በዚህም ከደረጃ በታች የሆኑና የጥራት ጉድለት ያላቸው እንዲሁም የአገልግሎት ጊዜያቸው ያበቃ የአፈር ማዳበሪያና የጥራት ደረጃቸው የማይታወቁ የፀረ አረም ኬሚካሎች አገልግሎት ላይ እንዳይወሉና እንዲወገዱ እንደሚደረግም ሃላፊው ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሀገር ውስጥ እየተመረቱ ያሉ ፈሳሽ ማዳበሪያዎች እውቅና ያላቸውና የተመዘገቡ መሆናቸውንና የጥራት ማረጋገጫ ከሚመለከተው አካል ያገኙ መሆናቸውን በስፋት እንደሚቆጣጠሩ አክለዋል።
አርሶ አደሩም ማንኛውንም የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ከህብረት ስራ ማህበራት፣ ከዩኒየኖችና ከአንድ ማዕከል የግብርና ግብዓት ግብይት ብቻ መግዛት እንደሚገባቸው አስገዝበዋል።
በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን በዚህ ላይ በሰጡት አስተያየት በዘንድሮው ዓመት በክልሉ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የተለያየ ሰብል ምርጥ ዘር ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚሆነው ምርጥ ዘር በክልል ደረጃ የሚቀርብ ሲሆን ቀሪው ሲ1፣ ሲ2 እና ሲ3 የተባሉ የምርጥ ዘር ዓይነቶች በአርሶ አደሩ ተባዝተው በመሰረታዊ ማህበራት በኩል ለማቅረብ መታቀዱን አመልክተዋል።