ቀጥታ፡

ከተፈቀደው ክብደት በላይ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ተመጣጣኝ ቅጣት ተግባራዊ ለማድረግ ጥናት እየተካሄደ ነው - የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2016(ኢዜአ)፦ከተፈቀደ ክብደት በላይ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች በመንገድ መሰረት ልማቶችና ደህንነት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ተመጣጣኝ ቅጣት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

ከፍተኛ በሆነ የህዝብና የመንግስት ሀብት የተገነቡ መንገዶች የታለመላቸውን አገልግሎት ሳይሰጡ በተለያየ ምክንያት ጉዳት ሲደርስባቸው ይስተዋላል።

የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ከሚጎዱና የአገልግሎት ጊዜያቸውን ከሚያሳጥሩ ምክንያቶች መካከል በከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚስተዋለው ከመጠን ያለፈ ጭነት መሆኑ ተጠቃሽ ነው።

በዚህም የተነሳ መንግስት በየዓመቱ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለመንገዶች ጥገና ለማውጣት ይገደዳል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከተፈቀደ መጠን በላይ ክብደት በመጫን በመንገድ ኃብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል በ14 ከተሞች የክብደት መለኪያ ሚዛን አዘጋጅቶ እየሰራ ይገኛል።

የከባድ ተሽከርካሪዎች የጭነት ሚዛን አገልግሎት ከሚሰጥባቸው መካከል የሱሉልታ ሚዛን ጣቢያ ይጠቀሳል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሱሉልታ ሚዛን ጣቢያ ሃላፊ ተሻለ ብርሃኑ፤ ጣቢያው በየቀኑ በርካታ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ሚዛን እንደሚለካ ተናግረዋል።

ነገር ግን ከተፈቀደላቸው ክብደት በላይ በሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ሳቢያ የመንገድና የድልድይ መሰረት ልማቶች ላይ ጉዳትና የትራፊክ አዳጋ መንስኤው እየሆኑ ነው ብለዋል።

ህግ ተላልፈው የተገኙ ተሽከርካሪዎች የጭነት መጠናቸውን እንዲያስተካክሉና ወደ ሌላ ተሽከርካሪ ቀንሰው እንዲያጓጉዙ ከማድረግ በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት እንደሚቀጡ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የተቀመጠው የቅጣት መጠን ተሽከርካሪዎች በሚጭኑት ክብደት የመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት አንጻር ዝቅተኛ ነው ብለዋል።


 

በሸገር ከተማ የመና አቢቹ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ደህንነት አስተባባሪ የሆኑት ኢንስፔክተር ደረሰ ሚደቅሳ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች በጣቢያው ገብተው እንዲመዘኑ በማድረግና ጣቢያውን ጥሶ ለማለፍ በሚፈልጉት ላይም የህግ ማስከበር ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከመጠን በላይ ክብደት የሚጭኑ የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች ከመንገድም አልፎ በዜጎች እና በራሳቸውም ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።


 

በሚዛን ጣቢያው ከመጠን በላይ ክብደት በመጫን ከተገኙት አሽከርካሪዎች መካከል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ እንደሚሉት የግምት ጭነት ችግር እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

አሽከርካሪዎቹ በጣቢያው ስለክብደት መጠንና ከክብደት በላይ መጫን የሚያስከትለውን ጉዳት ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልፀው፤ በቀጣይ በሚፈቀደው መጠን ለመጫን ጥረት እንደሚደርጉ ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ሀብት ዘርፍ አስተዳደር እና የኔትወርክ ማኔጅመንት ዳይሬክተር ኢንጅነር ኑሪዬ መሐመድ፤ ከመጠን በላይ በሚጭኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የመንገድ ብልሽት እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።

ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ መንገዶች ለብልሽት እየተዳረጉ የህዝብና የመንግስት ሀብት ለብክነት እየተጋለጠ ነው ብለዋል።

ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት 16 ሺህ ኪሎሜትር መንገድ ለመጠገን 12 ቢሊየን ብር በጀት መያዙን ገልፀው ይህም በከፍተኛ ክብደት የተነሳ በሚደርሰው ጉዳት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከክብደት በላይ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ላይ እየተጣለ ያለው ቅጣት አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተመጣጣኝ ቅጣት ተግባራዊ ለማድረግ ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ነው የገለጹት።

 

   

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም