በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል - ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል - ኮሚሽኑ
ዲላ፤የካቲት 18/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የማህበረሰብ ተወካዮች መረጣ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለፀ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በሰባት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተሳካ የተወካዮች መረጣ ማከናወን ተችሏል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ 12 ዞኖችም ከነገው ዕለት ጀምሮ በሁለት ቡድን የተከፈለ የተወካዮች መረጣ እንደሚከናወን በመግለጫው ጠቅሰዋል።
በመጀመሪያው ቡድን በጌዴኦ፣በጋሞ፣በጋርዱላ፣ በኮንሶ፣ በአሌ፣ በኮሬ እና በቡርጂ ዞኖች የሚካሄድ ሲሆን በነገው ዕለት ደግሞ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ይጀምራል ብለዋል።
ይኸው የተወካዮች መረጣ ለተከታታይ አራት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከተለያዩ ማህበራዊ መሠረቶች በተለይም ከወጣቶች፣ ከሴቶች፣ ከመንግሥት ሰራተኞች፣ ከንግዱ ማህበረሰብ የተውጣጡ ተወካዮች የሚሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።
"መረጣውም አካታችነት፣ ግልፀኝነት፣ አሳታፊነትና ተአማኒነት ያለው እንዲሆን ይደረጋል" ብለዋል።
የተወካዮች መረጣ የተሳካ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በተለይም የአካባቢው አስተዳደር እና ህብረተሰቡ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።