ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በጥናትና ምርምር የተደገፉ የግብርና ስራዎችን እየሰራ ነው

ቦንጋ ፤የካቲት 18/2016 (ኢዜአ)፦ በጥናትና ምርምር የተደገፉና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የግብርና ስራዎችን በተቀናጀ ሁኔታ እያከናወነ መሆኑን የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ገለፀ።

ዩኒቨርሲቲው የእንሰት ምርምር እና ተከላ ስራን የዓለም የምግብ ፕሮግራም የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በጌሻ የምርምር ማዕከል በይፋ አስጀምሯል።

በዚህ ወቅት የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር  ጴጥሮስ ወልደ ጊዮርጊስ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂና የክህሎት እገዛ ለማድረግ ከማህበረሰቡ ፍላጐት ጋር የሚጣጣም ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል።

 በዚህ ረገድ በአካባቢው ያለውን ዕምቅ የመልማት አቅም በምርምር በመደገፍ ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን የስራ ባህል ለመቀየር የሚያስችሉ  ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ከዋና ግቢው በተጨማሪ በካፋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች  የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚረዱ የሰብል ዝርያዎችን የመጠበቅና የዝርያ ማሻሻል ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ከነዚህም ውስጥ በአካባባቢው በምግብ ምንጭነት በሚያገለግለው የእንሰት ተክል ላይ ምርምር ለማካሄድ ከጌሻ  የምርምር ማዕከል ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን  ገልፀዋል።

እንሰት ላይ ከሚሰራው የምርምር እና የልማት ስራ ባሻገር የአመራረት ስልቱን ለማዘመንና ጉልበት ቆጣቢ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱንም አስረድተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር  ዶክተር ግርማ ጥላሁን ዩኒቨርሲቲው በዕውቀት ሽግግር፣ ክህሎትን በማሳደግና በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረተ አገልግሎት በመስጠት ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።


በዚህ ረገድ አሁን ላይ 17 የጥናትና ምርምር ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ከነዚህ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ከሚሰራው ስራ ባሻገር በቀጣይ በመማር ማስተማሩ ዘርፍ ራሱን የቻለ የምግብ ዋስትና ተቋም ለመክፈት ማቀዱን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ለምርመር የሚረዱና ከአካባቢው የአየር ንብረት ጋር ተስማሚ የሆኑ የእንሰት ዝርያዎችን የመትከል ስራ ከ3 ሺህ  ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ እንደሚሰራና በአንድ ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የማስጀመሪያ ችግኝ መተከሉን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አማካሪ አቶ ዮሐንስ መላኩ በበኩላቸው በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ገበያ መር ስብሎችን ለማልማት ለተያዘው ውጥን ዩኒቨርስቲው የቅርብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ከሰብል ምርቶች በተጨማሪ በእንሰት እና በስራ ስር ተክሎች ልማት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የእንሰት ልማት ለካፋ ማህበረሰብ የማንነቱ መገለጫ የምግብ ዋስትናው ማረጋገጫ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ልማቱ እየቀነሰ መምጣቱን የገለፁት ደግሞ የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደመላሽ ንጉሴ ናቸዉ።


አሁን በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረውን መልካም ተግባር  ወደ ዞን በማስፋት ተፈፃሚ ለማድረግ  ይሰራል ብለዋል።

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው አርሶ አደሮች አዳዲስ የግብርና አሰራሮችን በማስተማር ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን የተናገሩት የጌሻ ወረዳ ደኒቲ ቀበሌ አርሶ አደር አቶ ቆጭቶ አቱሞ ናቸው።


የአካባቢው  ማህበረሰብ  ዋነኛ የምግብ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግለው እንሰት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበሽታና በተባዮች እየተጠቃ የምርት መቀነስ እንዳመጣ ጠቁመው ይህን ችግር በሚፈታ መልኩ ዩኒቨርሲቲው የጀመረው ስራ ለአርሶ አደሩ ተስፋን የሚያጭር መሆኑን አስረድተዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሞዲዚ እና ሌሎችም የድርጅቱ ባለሙያዎች ፣ የክልልና የዞን አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው የስራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

 
  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም