ቀጥታ፡

 በአትክልትና ፍራፍሬዎች ላይ የታየው የዋጋ ቅናሽ  በሰብል እና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይም እውን እንዲሆን መስራት  ይገባል 

አዲስ አበባ ፤የካቲት 18/2016(ኢዜአ)፦በእሁድ ገበያዎች በአትክልትና ፍራፍሬዎች ላይ የታየው የዋጋ ቅናሽ  በሰብል እና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይም   እውን አንዲሆን መስራት ይገባል ሲሉ ሸማቾች ገለፁ፡፡

በአዲስ አበባ ገበያን በማረጋጋት የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ ታስበው ከተጀመሩ ስራዎች መካከል አንዱ የእሁድ ገበያን በየአካባቢው ማስፋፋት ነው፡፡

የእሁድ ገበያዎች ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የምግብ ፍጆታቸውን እንዲያገኙ እድል መፈጠሩ በተጨባጭ እየታየ መጥቷል፡፡

በተለይ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን የግብርናና ምርቶች ዋጋ ለማረጋጋት ጉልህ ሚና እየተወጣ  ይገኛል። 

ኢዜአ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ሸማቾች እንዳሉት የእሁድ ገበያ የዋጋ ንረትን በማረጋጋትና የኑሮ ጫናን በመቀነስ ረገድ ጉልህ አበርክቶ አለው፡፡ 


በገበያዎቹ ያለውን የምርት አቅርቦት በማሻሻል፣እንዲሁም ሸማቹና አምራቹን በቀጥታ በማገናኘት ግብይት እንዲፈጽሙ በማድረግ የዋጋ መረጋጋት ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

በእሁድ ገበያዎች ያለው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ዋጋ ተመጣጣኝ እንዲሁም የሸማቹን አቅም ያገናዘበ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ሸማቾቹ በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ የታየውን የዋጋ ቅናሽ በሰብል እና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ማስፋት ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይም የጤፍና የጥራጥሬ ምርቶች ዋጋ ቶሎ ቶሎ እየጨመረ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ችግሩን የሚቀርፍ ማስተካከያ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች በበኩላቸው ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ በበኩላቸው፤ የእሁድ ገበያዎች የታለመላቸውን ግብ እንዲያሳኩ ከቢሮ ጀምሮ እስከታች ወረዳ ድረስ ባለሙያዎችን በመመደብ ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 


ይህን ተከትሎ አሁን ላይ በአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የዋጋ መሻሻሎች እየተስተዋሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቢሮው በሰብልና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ መናር  ለመቀነስ የገበያ ማዕከላትን ለማስፋትና የምርት አቅርቦትን ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም