ቀጥታ፡

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ወጥ የሆነ የፍልሰት አስተዳደር ስርዓትና የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር አገራቱ በትብብር  መስራት ይጠበቅባቸዋል

አዲስ አበባ ፤የካቲት 18/2016(ኢዜአ)፦በምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ወጥ የሆነ የፍልሰት አስተዳደር ስርዓትና የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር አገራቱ በትብብር  መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

የምስራቅ አፍሪካ አገራት ቀጣናዊ የፍልሰት ጉዳዮች የሚኒስትሮች ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር የቀጣናው አባል አገራት፣ የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት /አይ ኦ ኤም/፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስትታት /ኢጋድ/ እና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

መድረኩ  የቀጣናው አባል አገራት በሰራተኛና ፍልሰት አስተዳደር ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክሩበት እንደሚሆን ተገልጿል።

በቀጣናው የሚስተዋለውን ከፍተኛ ፍልሰት ለመቆጣጠር በፖሊሲ የተደገፈ ምክረ ሃሳብ ለማስቀመጥ የሚያስችል መሆኑም ታውቋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳንኤል ተሬሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያለውን የፍልሰተኞች አስተዳደር እውን እንዲሆን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

ላለፉት ሁለት ዓመታት አስራ አንድ  አባል አገራትን ያቀፈውን ቀጣናዊ የፍልሰት ጉዳዮች የሚኒስትሮች ፎረም ስትመራ መቆየቷን አንስተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በቀጣናው የሚስተዋለውን አስቸጋሪ የፍልሰተኞች ምጣኔ ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የሚቻልበትን ልምድ ስታጋራ የቆየች መሆኑንም አንስተዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ እንደ አባል አገር በሚጠበቀው ልክ የቀጣናውን የፍልሰተኞች ተግዳሮት ለመቅረፍ የበኩሏን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

አባል አገራቱም በትብብር መንፈስ  መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።


 

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ ግንኙነት ስራ አስፈጻሚና የፎረሙ የኮሚቴ አባል ዶክተር አያሌው ተካልኝ በበኩላቸው ፣በቀጣናው ኢትዮጵያ ሰፊ የፍልሰተኞች ቁጥር የምታስተናግድ መሆኗን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሻለ የፍልሰት አስተዳደር እንዲፈጠር፣ የፍልሰተኞችና የስደተኞችን መብት ለማስከበርና መሰል ተግባራት ላይ ስትሰራ የቆየችባቸው ተግባራት ሰፊ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም በምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ወጥ የሆነ የፍልሰት አስተዳደር ስርዓትና የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር አገራቱ በትብብር  መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።


 

የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቶው ዋኔ በበኩላቸው፣ የፍልሰተኞች ጉዳይ ለቀጣናው ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል።

በዚህም በዘርፉ ከቀጣናው የሚጠበቀውን ውጤት ለማግኘት አለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የበኩሉን ድጋፍ  እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሚዘልቀው መድረክ ኢትዮጵያን ጨምሮ ፣የሶማሊያ ፣ የሱዳን ፣ የደቡብ ሱዳን ፣የኡጋንዳ፣ የሩዋንዳ፣ የታንዛኒያ፣ የብሩንዲ፣ የኤርትራና  የጅቡቲ  ተወካዮች እየተሳተፉ ነው::

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም