ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የወላይታ ዞን ተወካዮችን መረጣ ከነገ ጀምሮ ያካሂዳል - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የወላይታ ዞን ተወካዮችን መረጣ ከነገ ጀምሮ ያካሂዳል
ሶዶ፤የካቲት18/2016(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከወላይታ ዞን በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የማህብረሰብ ተወካዮችን መረጣ ከነገ ጀምሮ እንደሚያካሂድ አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮች የመምረጥ ሂደትና ሌሎች የሚያከናውናቸው ተግባራትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በመግለጫው እንዳሉት፣ ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለምክክሩ አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ የማህበረሰብ ተወካዮችን ሲያስመርጥ ቆይቷል።
"እስካሁን ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በሰባት ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተሳካ የተወካዮች መረጣ አከናውኗል" ብለዋል።
ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የወላይታ ዞን የማህበረሰብ ተወካዮችን መረጣም ከነገ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል።
በዚህም በዞኑ ከሚገኙ 23 ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚቀርቡትን አጀንዳዎች የሚሰበስቡ ተወካዮች መረጣ እንደሚከናወን አስረድተዋል።
በተወካዮች መረጣው ላይ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሳተፉ ሲሆን የሚወክሏቸውም ሴቶችና ወጣቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ አርሶ አደሮች፣ እድሮች እንዲሁም የተለያዩ የመንግስት ሠራተኞች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የተወካዮች መረጣ ሂደት የተሳካ እንዲሆን የዞኑ አስተዳደርና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ዶክተር ዮናስ ጥሪ አቅርበዋል።