በህንድ አንድ እቃ ጫኝ ባቡር ያለ አሽከርካሪ 70 ኪሎ ሜትሮች መጓዙ ተነገረ

1121

አዲስ አበባ ፤የካቲት 18/2016 (ኢዜአ)፦በህንድ አንድ እቃ ጫኝ ባቡር ያለ አሽከርካሪ 70 ኪሎ ሜትሮች መጓዙን ተከትሎ የሀገሪቱ የባቡር አስተዳደር ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።

በህንድ አንድ እቃ ጫኝ ባቡር ያለ አሽከርካሪ መንቀሳቀሱን የሚያሳዩ  ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኗል።

የህንድ የባቡር አስተዳደር ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ መነሻውን ከካሽሚር ግዛት ወደ ጃሙ ያደረገ እቃ ጫኝ ባቡር ያለ አሽከርካሪ እሁድ ከቀኑ 7፡15 እስከ ቀኑ 9 ሰዓት ድረስ መጓዙን ተናግረዋል።

በ53 ፍርጎዎች ለቤትና መንገድ ግንባታ የሚያገለግሉ የድንጋይ ጠጠሮችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረው ባቡሩ በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር ፍጥነት እንደነበረውም ተነግሯል።

ሆኖም በሰው ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳያደርስ ባቡሩን ማስቆም እንደተቻለ ነው ሃላፊዎቹ የገለጹት።

በካቱሃ ግዛት የአሽከርካሪዎችና ባለሙያዎች ቅይይር ሲደረግ ችግሩ ሊፈጠር እንደቻለ የተነገረ ሲሆን 70 ኪሎ ሜትሮችን ያለ አሽከርካሪ እንዴት ሊጓዝ ቻለ የሚለው ጉዳይ ላይ በጥብቅ ምርመራ እንደሚደረግ ቢቢሲ ዘግቧል።

የቁጥጥር ባለሙያዎች ባቡሩን ለማስቆም የዛፍ ግንዶች እንደተጠቀሙ ያስነበበው ዘገባው በዚህም የባቡሩን ፍጥነት በመቀነስና በካቱሃ ግዛት እንዲቆም መደረጉን አስነብቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም