ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥና በጋራ የመልማት ፍላጎትን የሚያሳካ ነው

ሶዶ፤ የካቲት 18/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ በአካባቢው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥና ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት ፍላጎትን የሚያሳካ ነው ሲሉ ምሁራን ገለፁ።

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ በአካባቢው የጋራ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባሻገር ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት ፍላጎትን እውን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ። 

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አበሻ ሽርኮ፤ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት ፍላጎትን እውን በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው። 

"የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከጎረቤት ሀገራት ጋር አብሮ የመልማትና የማደግ ፍላጎትን የሚያበረታታ መሆኑን አውስተው ሁላችንም በጉዳዩ ላይ የጋራ አቋም በመያዝ ለመጪው ትውልድ መሠረት ልንጥል ይገባል" ብለዋል። 

''ከታሪክ አኳያ ለበርካታ ዘመናት የባሕር በር ስንጠቀም የነበርን ሀገር በመሆናችን የባሕር በር የማግኘት ታሪካዊ መብት አለን'' ያሉት ምሁሩ የባህር በርን ማግኘት ዘርፈ ብዙ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ እንዳለውም አብራርተዋል።  

"የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ከታሪካዊ ዳራው፣ ከምጣኔ ሀብትና ከህዝቡ ቁጥር እድገት እንዲሁም ከከባቢያዊ ሁኔታ አንጻር ተገቢነት ያለው መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል" ብለዋል። 

በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ ትምህርት ክፍል መምህርና የቅድመ ምረቃ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር አቶ እሸቱ ተስፋዬ በበኩላቸው የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። 

"ኢትዮጵያ የጥንት ስልጣኔ አሻራ ለዓለም ያበረከተች፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ብሎም 3ኛዋ የዓለማችን ከፍተኛ የዲፕሎማት መቀመጫ ሀገር እንደመሆኗ ብሔራዊ ጥቅሟን ማጣቷ ተገቢ አይደለም" ብለዋል። 

በዓለማችን 44 የሚሆኑ ሀገራት ወደብ አልባ ቢሆኑም ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋን ተገቢነት ያረጋግጣል ብለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም