ቀጥታ፡

13ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባኤ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2016 (ኢዜአ)፦13ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባኤ ዛሬ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መዲና አቡዳቢ  ጀምሯል።

በድርጅቱ የታዛቢነት መቀመጫ ያላት ኢትዮጵያም በጉባኤው ላይ እየተሳተፈች ነው።

''በንግድ ለሕዝብ መድረስ '' በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የዓለም የንግድ ድርጅት የ164 አባል ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትርና የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ተደራዳሪ ገብረመስቀል ጫላ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ኡመር ሁሴን ኢትዮጵያን ወክለው በጉባኤው ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።


 

ጉባኤው የባለብዙ ወገን የንግድ ስርዓት፣ የዓለም የንግድ ድርጅት ተቋማዊ ማሻሻያ እንዲሁም የቀረጥና የታክስ ስርዓት ማሻሻያዎችና የምግብ ዋስትናን ጨምሮ ሌሎች ዓለምን እየፈተኑ ባሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።

ንግድና ዘላቂ ልማት ፣የኢንዱስትሪ ልማት፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ ዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓት፣ ግብርናና የአሳ ሀብት ልማት የድጎማ ማዕቀፍ ውይይት የሚደረግባቸው ሌሎች  አጀንዳዎች ናቸው። 

በተጀመረው ጉባኤ የኮሞሮስና ቲሞር የአባልነት ጥያቄ አጽድቋል።

ኢትዮጵያ  የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየሰራች መሆኑን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን በድርድር አባል ለመሆን በታዛቢነት መሳተፍ የጀመረችው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2003 ነበር።

13ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባኤ እስከ የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም