ለመጪው ትውልድ እዳን ሳይሆን ምንዳን ለማውረስ በመንግስት ቁርጠኛ አቋም ተወስዶ እየተሰራ ነው- ዶክተር ፍጹም አሰፋ - ኢዜአ አማርኛ
ለመጪው ትውልድ እዳን ሳይሆን ምንዳን ለማውረስ በመንግስት ቁርጠኛ አቋም ተወስዶ እየተሰራ ነው- ዶክተር ፍጹም አሰፋ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2016(ኢዜአ)፦ ለመጪው ትውልድ እዳን ሳይሆን ምንዳን ለማውረስ በመንግስት ቁርጠኛ አቋም ተወስዶ እየተሰራ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ "ሀብት የመፍጠር ጉዟችን፤ ያገጠሙ ተግዳሮቶችና የቀጣይ አቅጣጫዎች" በሚል መሪ ሃሳብ ህዝባዊ ውይይት ተካሒዷል፡፡
በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ ጥራቱ በየነ መርተውታል፡፡
ከክፍለ ከተማው ሁሉም ወረዳዎች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት መድረክ በለውጡ አመታት የተከናወኑ ስኬታማ ተግባራት እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮች በስፋት ተነስተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በለውጡ አመታት በመዲናዋ በተከናወኑ የልማት ስራዎችን አድንቀው ችግሮች ያሏቸውንም ዘርዝረዋል።፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ ከተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ባለፉት አምስት አመታት መንግስት የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙትም ችግሮቹን ተቋቁሞ ያከናወናቸው የልማት ስራዎች የሚያኮሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በግብርናው ዘርፍ በተለይም በስንዴ ምርት ላይ የመጣው ለውጥና የተመዘገበው ውጤት ታሪካዊ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያን ከተመጽዋችነት በመውጣት ራስን ወደ መቻል በመሸጋገር ላይ መሆኗን ገልጸው የተሸጋገሩ እዳዎች እየተከፈሉ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ከባለፈው ጊዜ ከተወረሰው እዳ ውስጥ 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ብድር መክፈል ተችሏል ብለዋል።
በሁሉም መስክ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ለመጪው ትውልድ እዳን ሳይሆን ምንዳን ለማውረስ በመንግስት ቁርጠኛ አቋም ተወስዶ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ፤ የሰላምና ጸጥታ ማስጠበቅ ጉዳይ የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም መንግስት ለሰላም በሩን ክፍት ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ ጸጥታን የማስከበር ስራ ግን አሁንም ተሳትፎና ትብብር የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ ጥራቱ በየነ፤ ከለውጡ ወዲህ በመዲናዊ በርካታ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ከሰላም አኳያም ከፀጥታ መዋቅሩ በተጨማሪ ህዝባዊ የሰላም ሠራዊቱን በማሳተፍ በመዲናዋ ሊፈጸሙ የነበሩ ወንጀሎችን በማክሸፍ ወንጀለኞችንም መያዝ መቻሉን ጠቅሰዋል።