የከተሞች ፎረም መዘጋጀቱ ችግር ፈቺ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎቻችንን ለማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሮልናል - ተሳታፊዎች

418

ሶዶ፤ የካቲት 17/2016(ኢዜአ)፦ በዘጠነኛው የከተሞች ፎረም ላይ መሳተፋቸው የህብረተሰቡን ችግር የሚያቃልሉ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው በፎረሙ ላይ የተሳተፉ ሥራ ፈጣሪዎች ገለጹ።

ከየካቲት 9 እስከ 15/2016 በወላይታ ሶዶ በተካሄደው 9ኛው የከተሞች ፎረም ላይ የተሳተፉ ሥራ ፈጣሪዎች እንደገለጹት በፎረሙ የተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች መሳተፋቸው አብሮነትን ለማጠናከር የሚያስችል ነው።

የህብረተሰቡን ችግር የሚያቃልሉ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ ፎረሙ የተሻለ ዕድል እንደፈጠረላቸውም ለኢዜአ ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ሥራ ፈጣሪዎች መካከል የወራቤ ከተማ ነዋሪው አቶ ረሻድ ከድር በእናቶች እና አርሶ አደሮች ላይ የሚስተዋለውን የሥራ ጫና ማቃለል የሚያስችል የእንሰትና የቆጮ መፋቂያ፣ የጤፍ መውቂያ እንዲሁም የቃጫ ማምረቻ ማሽኖች ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።


 

ይህም የፈጠራ ሥራዎቻችንን ለማስተዋወቅ የተሻለ እድል ፈጥሮልናል ሲሉም ገልጸዋል።

በወላይታ ዞን የአረካ ከተማ ነዋሪውና በአውደ ርዕዩ ላይ የሰራውን መኪና ይዞ የቀረበው ወጣት አጃዬ ማጆር በበኩሉ ፎረሙ ያለንን የፈጠራ ውጤት ለሌሎች ለማስተዋወቅ ረድቶናል ብሏል።


 

የባለ ሁለት እግር ሞተር ሳይክል ሞተርን በመጠቀም መኪናውን እንደሰራ የተናገረው ወጣቱ፣ የፈጠራ ሥራዎች እየተጠናከረ መምጣት የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረት ባለፈ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እነደሚያስችልም አክሏል።


 

በ8ኛው የከተሞች ፎረም ላይ በፈጠራ የተሰሩ መኪኖች ለእይታ እንዳልቀረቡ ያስታወሰው ወጣት አጃዬ፣ ዘንድሮ ለ9ኛ ጊዜ በተካሄደው የከተሞች ፎረም ላይ የተለያዩ መኪኖች ቀርበው መመልከቱን ተናግሯል።

የፈጠራ ሥራዎች እያደጉ መምጣት ሥራ ፈጣሪዎችን በማነቃቃት ሀገራዊ አድገትን ለማፋጠን የራሱ ጠቀሜታ እንዳለውም ጠቁሟል።

ፎረሙ ከተሞች ያላቸውን ሀብትና የሥራ ፈጠራ ውጤት እንዲያስተዋውቁ እድል መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪው አቶ ዳዊት አብርሃም ናቸው።


 

በአካባቢው በስፋት የሚመረተውን የሙዝ ምርት ወደ ዱቄት፣ ገንፎ፣ ኬክና ሌሎች ጣፋጭ ምግቦች እንዲሁም ኮባውን ወደ ቃጫነት ቀይሮ የሚሰራ ማሽን ሰርተው ፎረሙ ላይ ለእይታ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት ከእንሰት ውጤት ይገኝ የነበረውን ቃጫ በአሁኑ ወቅት ከሙዝ እያመረቱ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዳዊት፣ ፎረሙ ይሄንና አዳዲስ ፈጠራዎችን ከማቅረብ ባለፈ ሥራ ፈጣሪዎችን እርስ በእርስ ያስተዋወቀ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተሞች ፎረም "የዘመኑ ከተሞች ለኢትዮጵያ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ ከየካቲት 9 እስከ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በርካታ ከተሞች በተሳተፉበት በወላይታ ሶዶ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም