በሲዳማ ክልል እየተከናወነ ባለ የተፋሰስ ልማት ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል--ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል እየተከናወነ ባለ የተፋሰስ ልማት ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል--ቢሮው
ሀዋሳ ፤ የካቲት 17/2016(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል እየተከናወነ ባለው የተፋሰስ ልማት ሥራ አስካሁን ድረስ ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ በተፋሰስ የሚለማውን መሬት በዕጽዋት ለመሸፈን 300 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የማፍላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በ646 ንዑስ ተፋሰሶች 126 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።
ለልማቱ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የገለጹት ቢሮ ሃላፊው በልማቱም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት 21 ቀናት በተለያዩ ንዑስ ተፋሰሶች በተካሄደ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ዘመቻም የዕቅዱን 80 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስታውሰዋል::
በልማት ሥራው ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል የአፈርና የድንጋይ እርከን፣ የተጎዳ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ የመከለል፣ የጎርፍ መቀልበሻ ጋቢዮን ሥራና ሌሎችም ይገኙበታል ብለዋል።
በተለይ በስምንት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጠረጴዛማ እርከን በልዩ ትኩረት ለማከናወን ታቅዶ በአሁኑ ወቅት 30 በመቶ መከናወኑን ጠቁመዋል።
በህዝብ ተሳትፎ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት በተካሄደባቸው አካባቢዎች በመጪው ክረምት የሚተከሉ 300 ሚሊዮን ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑንም ቢሮው ኃላፊ አስታውቀዋል።
በተለዩ 302 ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች እስካሁን ድረስ 176 ሚሊዮን ችግኝ ለማፍላት መቻሉንም ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ከተፋሰስ ልማት ጋር በማስተሳሰር የባህር ዛፍ ተክልን በመንቀል በምትኩ ቡና፣ እንሰትና የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል በየደረጃው በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በማእከላዊ ሲዳማ ክልል የሎካ አባያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሻምበል ሀግርሶ በበኩላቸው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራን የወረዳው ህዝብ ባህሉ እያደረገው መምጣቱን አስረድተዋል።
በተለይም ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ቀደም ሲል በአካባቢው ይከሰት የነበረውን የአፈር መሸርሸርና መሠል ችግሮች በመፍታት ምርትና ምርታማነት ማሳደጉን ገልጸዋል።
በወረዳው በዚህ ዓመት 5 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ 96 ፐርሰንት ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ፎና በበኩላቸው በወረዳው ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በተለያዩ ምክንያቶች ለጉዳት የተጋለጡ ስፍራዎች ማገገም እንደቻሉ ገልጸዋል።
በዚህ ዓመትም በ4 ሺህ 655 ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ሥራ ለማከናወን ታቅዶ ሙሉ ለሙሉ አሳክተናል ብለዋል።
የተፋሰስ ሥራውን በአረንጓዴ ልማት ለማጠናከር በወረዳው እየተዘጋጁ ካሉ ከ7 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆነው ችግኝ ከሰውና እንስሳት ንክኪ በተከለሉ ሥፍራዎች እንደሚተከልም አስረድተዋል።