ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት አገልግሎት ጥልቅና አስደናቂ አሻራዎችን የሰነደ እምቅ የሀገር ሃብትና የእውቀት ማእድ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት አገልግሎት ጥልቅና አስደናቂ አሻራዎችን የሰነደ እምቅ የሀገር ሃብትና የእውቀት ማእድ መሆኑ ተገለጸ።

አንጋፋው የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል።

የሚሰጠውን አገልግሎት ማስፋት የሚያስችለውን ባለ 17 ወለል አዲስ ሕንጻ በትናንትናው እለት አስመርቋል።


 

በእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ፣ ታሪክና ሥነ ፅሁፍ ጉዳዮች ተመራማሪ ዶክተር ግርማ ጌታሁን፤ የቀድሞው ወመዘክር፣ ከልጅነት ጀምሮ ራሴን ከዕውቀት ጋር ያቆራኘሁበት ተቋም ነው በማለት ያስታውሱታል።

ከሀገር ከወጡ ረጅም ዓመታት ቢያስቆጥሩም በልጅነታቸው የእውቀት ማዕድ የተቋደሱበትን የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዛሬም ተመለልሰው ይገለገሉበታል።

የኢትዮጵያ የስነ ፅሁፍ ሃብቶች ተሰንደውና ተጠብቀው ለትውልድ የሚተላለፉበት ወመዘክር ለሀገር ሰፊ የታሪክ አሻራ እና የእውቀት ማእድ ስለመሆኑ ይናገራሉ።


 

የሥነ ሕይወት ሊቁ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፤ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ትውልድ የሚታነጽበት የእውቀት ቋት መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ለተመራማሪዎች ጥናት፣ ለታዳጊዎች ሰፊ የእውቀት ማእድ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል።

ተቋሙ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ መዛግብትንና ሰነዶችን በማሰባሰብ ተደራሸነቱን ማስፋት አለበት ሲሉም አክለዋል።


 

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፍ ማህበራት ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩ፤ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት አገልግሎት ከሰነዳቸው ሀብቶች መካከል የዘመናዊ ሙዚቃ ስራዎች እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የኪነ ጥበብ ዘርፍ ስራዎች በመሰነድ ለጥናትና ምርምር እንዲውሉ በማድረግም ትልቅ ሚና እንዳለው አንስተዋል።


 

ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ የቁም ፅህፈት መፃፍ የጀመሩትና በአገልግሎቱ በብራና ፅሁፎችን በመጻፍ ሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ ለትውልድ እንዲተላለፍ እያደረጉ ያሉት ቄስ ፈቃዴ ቢሻው፤ አገልግሎቱ ለትውልድ የሚሸጋገሩ የሀገር ሃብቶችን ሰንዶ መያዙን ገልጸዋል።


 

በተመሳሳይ እስላማዊ የብራና ፅሁፎችን አስጎብኚ የሆኑት አብደልራሲ ሀጂ መሀመድ አሚን፤ አገልግሎቱ በመጥፋት ላይ የሚገኙ እስላማዊ ታሪካዊ ቅርሶችን በመሰነድ ትልቅ ውለታ የዋለ ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል።

በመጥፋት ላይ የሚገኙ ቅርሶችን ቅጂዎችን በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ወደ ዲጂታላይዜሸን በመለወጥ የጽሁፍ ሀብቶቹ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም