የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተደራሽነቱን ለማጠናከር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተደራሽነቱን ለማጠናከር እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የመስኩን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተደራሽነቱን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ያስገነባው ለቤተ መዛግብት አገልግሎት የሚውል ባለ 17 ወለል አዲስ ሕንፃ ዛሬ አስመርቋል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት፤ ተቋሙም የኢትዮጵያን መንፈሳዊ፣ ቁሳዊ፣ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ትሩፋቶችን ከትበው፣ ሁነትን መዝግበው፣ ጥበብና ዕውቀትን አስፍረው የያዙ ጽሑፍና የቃል ታሪካዊ ቅርሶች ለማስተላለፍ ትልቅ አበርክቶ አለው።
ከ80 ዓመታት በፊት የተቋቋመው አገልግሎቱ ትልቅ ከፍታ ላይ መድረሱን ገልፀው፣ አገልግሎቱ የመረጃ ሃብቶች በማደራጀት፣ በመንከባከብና በመጠበቅ ለትምህርት ጥናትና ምርምር እንዲውሉ በማድረግና ለትውልድ በመዘከር ለአገር ትልቅ ውለታ መዋሉንም ገልፀዋል።
አዲሱ ህንፃም ተቋሙን ይበልጥ በማጎልበት፣ በቴክኖሎጂ በማዘመንና መረጃዎቹን በሳይንሳዊ ዘዴ በመጠበቅ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት መካከል አንዱ እንዲሆን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
የልዩ የመዛግብትና የጽሑፍ ቅርሶች መጠበቂያና ማደራጃ በመሆን ተልዕኮውን ዕውን እንዲያደርግ ለማድረግ ሚኒስቴሩ እንደ ተጠሪ ተቋምነቱ ለአገልግሎቱ መዘመን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
ለአገልግሎቱ ባደረጉት ትልቅ አበርክቶ ዕውቅና ከተሰጣቸው መካከል ለሕንፃው ግንባታ እንዲጀመር ያደረጉት የቀድሞው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር አሚን አብዱልቃድር ይገኙበታል።
አምሳደሩ ለኢዜአ እንደተናገሩት ተቋሙ የኢትዮጵያን የዘመናት ታሪክ በመሰነድ ለትውልድ ለማሻገር ካለው ትልቅ ተልዕኮ አኳያ አገልግሎቱን ለማስፋት ልምድና ተሞክሮ ተወስዶ ግንባታው እንደተጀመረ ገልጸዋል።
ከሕንፃ ግንባታ ባሻገር ደግሞ የተሰባሰቡ ሃብቶችን በዘመናዊ መንገድ በዲጂታላይዜሽን ተደራሽ እንዲሆኑ ማስቻልና ለትውልድ ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
ተቋሙ ወደፊትም በክልሎችም ተደራሽነቱን በማስፋትና ሰነዶችን በማሰባሰብ ላይ ይበልጥ መስራት እንዳለበትም ነው ያነሱት።
ለብዙ ዓመታት ተቋሙን በተለያዩ ሃላፊነቶች ያገለገሉት የቀድሞ የቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍቱ ሰራተኞች መካከል አቶ ወልደስላሴ ሽመልስና አቶ አምታታው ርዳው ይገኙበታል።
ተቋሙ ባለፈባቸው ዘመናት ለአገር ግንባታና ትውልድ ማነፅ ትልቅ አበርክቶ እንደነበረው ገልጸዋል።
አገልግሎቱ ለትውልድ ግንባታ ካለው ፋይዳ አኳያ በቀጣይም በየክልሉ መዛግብትን ማሰባሰብና በዘመን አፈራሽ አማራጮች ተደራሽነቱን ማስፋት እንዳለበት ተናግረዋል።