ቀጥታ፡

የአፋር ሴት ነጋዴዎች ማህበርን ለማጠናከር ድጋፍ ይደረጋል- የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበር

ሠመራ ፤ የካቲት 16 / 2016(ኢዜአ) ፡- የአፋር   ሴት ነጋዴዎችን ለማጠናከር   አስፈላጊውን   ድጋፍ  እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበር  ገለጸ። 

የአፋር ሴት ነጋዴዎች ማህበር ለማጠናከር የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ዛሬ በሠመራ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት  የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበር  ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ እንዳሉት፤  ሴቶች ከተመቻቸላቸው አቅማቸውን አውጥተው በመጠቀም ለውጥ ማምጣት  ይችላሉ።

የአፋር ሴቶች የክልሉን  የተፈጥሮ ፀጋ ተጠቅመው መልማት እንደሚችሉ  ጠቅሰው ትንሽ ድጋፍና እገዛ ከተደረገላቸው አቅማቸውን ተጠቅመው ለሌሎች ጭምር የሚተርፉ በመሆናቸው ማህበራቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የአፋር  ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አሚና ያሲን በበኩላቸው ፤ ማህበሩ ዋና ከተማ ላይ ብቻ ሳይወሰን እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ በመውረድ  ሴቶችን የማብቃት  ስራ እንሰራለን ብለዋል።

በመንግስት ትኩረት አግኝተው  ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የክልሉ ንግድ ገበያ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ መሐመድ ሁመድ ፤  በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች ሊበረታቱ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ማህበሩን ለማጠናከር የተዘጋጀው መድረክ ሴቶችን በመደገፍ  በመረጡት የንግድ ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ በቀጣይ ብድር   ለማመቻቸት እንደሚሰራ  አስረድተዋል።

ሴቶች እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነትና የጓዳውን ችግር ከሌላው በተሻለ የሚረዱ በመሆናቸው የነጋዴው ማህበር መጠናከር አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው አብራርተዋል።

በመጨረሻም ማህበሩን ያጠናክራሉ ተብለው የታመነባቸው አዲስ አስር አባላት የተመረጡ ሲሆን፤ ወይዘሮ አሚና ያሲንን በፕሬዚዳንትነት ተሰይመዋል።

በምክትልነት ወይዘሮ ሐስና ሐቢብና በፀሃፊነት ደግሞ ወይዘሮ ስዓዳ ሐቢብ እንዲሁም ገንዘብ ያዥና ሒሳብ ሹም ሆነው እንዲያገለግሉ ተመድበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም