ቀጥታ፡

የድሬዳዋ ምድር ባቡር ተርሚናል ታሪካዊ ቅርስነቱን በጠበቀ መልኩ ሊጠገን ነው

ድሬዳዋ፤ የካቲት16/2016(ኢዜአ)፦ አንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረው የድሬዳዋ ምድር ባቡር ተርሚናል ታሪካዊ ቅርስነቱን በጠበቀ መልኩ በ13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ጥገና ለማካሄድ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን፣ የድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤትና ስራውን የሚያከናውነው የሰለሞን ኮንስትራክሽን ድርጅት  ናቸው።  

የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሐይሉ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ በአገሪቷ ታሪካዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ ከቱሪዝም ዘርፍ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።  


 

የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶችና ሃብቶችን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ቅርሶችን በተገቢው መንገድ የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የመጠገን ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

ታሪካዊ ቅርስነቱን እንደጠበቀ ባለስልጣኑ በመደበው 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ለመጠገን ውል የተገባለት የድሬዳዋ የምድር ባቡር ተርሚናል በውስጡ በርካታ ታሪካዊ ሃብቶችን ያቀፈ የትራንስፖርት ቱሪዝም ዘርፍ ግንባር ቀደም ቅርስ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ዘመን የተሻገረው የድሬዳዋ ባቡር ትራንስፖርት ለከተማዋ መሠረት የጣለና ልዩ መገለጫዋ ነው። 

ስራውን የሚያከናውነው ድርጅት ቅርስነቱንና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ ጥገናውን አካሂዶ በዘጠኝ ወር ውስጥ አጠናቆ እንደሚያስረክብ አረጋግጧል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም