ዩኒቨርሲቲዎች የአምራች ዘርፉ የሚፈልገውን የሰው ኃይል ማፍራት ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2016(ኢዜአ)፦ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአምራች ኢንዱስትሪ ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ማፍራት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሁለተኛው አገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ፎረም "የዩንቨርሲቲ፣ኢንዱስትሪና የመንግስት የሶስትዮሽ ትብብር፤ ለፈጠራና ቴክኖሎጂ ልማት አንቀሳቃሽ ነው" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ የካይዘን ልህቀት ማዕከል ተካሄዷል።

ፎረሙን ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በጋራ አዘጋጅተውታል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግብዓትና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝና የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ (ዶ/ር)፣ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግብዓትና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ ሚኒስቴሩ የአምራች ኢንዱስትሪውን አቅም ለማጎልበትና የስራ ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይልን ለማፍራት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት የሚቻለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር በሚፈለገው ልክ መፍታት ሲችሉ ነው ብለዋል።

ለዚህም የትምህርት ተቋማቱ በአምራች ኢንዱስትሪው አቅም የማሳደግ ስራ ላይ ገቢራዊ የሚሆኑ ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶች ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተለይም አገር በቀል የፈጠራ ስራዎችን በማሳደግና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ሽግግርን ማፋጠን ላይ አበክረው እንዲሰሩም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠየቁት።


 

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የአምራች ኢንዱስትሪን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከመንግስትና ከኢንዱስትሪ አምራቾች ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ከዚህ አኳያ ተማሪዎች ከንድፈ ሀሳብ ትምህርት ባሻገር  በኢንዱስትሪዎች ገብተው የተግባር ትምህርቱን እንዲያገኙና የስራ ባህሉን እንዲለምዱ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በፎረሙ ላይ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት የተመለከቱ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በተጨማሪም ከፎረሙ ጎን ለጎን የአምራች ኢንዱስትሪውን ስራዎች የሚያሳይ አውደ ርዕይ ተካሄዷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም