ቀጥታ፡

ባንኮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን አቅም ለመፍጠር የሚያከናውኑትን ተግባራት ማጠናከር አለባቸው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2016(ኢዜአ)፦ ባንኮች በዓለም አቀፍ ደረጃ በፋይናንስ ዘርፉ ካሉ ተቋማት ጋር ብቁ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን አቅም ለመፍጠር የሚያከናውኑትን ተግባራት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥሪ አቀረበ። 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን በአገሪቱ የጀመረበትን የሲቢኢ ኑር 10ኛ ዓመቱን በዓል የመዝጊያ መርኃ ግብር አካሂዷል። 


 

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ፤ መንግሥት በአገሪቱ ያለውን የፋይናንስ ተደራሽነትና አካታችነት ለማረጋገጥ ከሚሰራባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ነው ብለዋል። 

በኢትዮጵያ አካታችና የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ለማጠናከር፣ በአገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማሳለጥ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የራሱ አስተዋጽዖ አለው ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት እንደ አገር በፋይናንስ ዘርፉ ላይ በተደረገው ማሻሻያዎች የወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በማጠናከር ረገድ አበረታች ለውጦች እንዲታዩ አድርጓል ነው ያሉት።

በቀጣይም ባንኮች የወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ቀልጣፋነትና ተደራሽነት ለማጎልበት የሚያከናውኑትን ተግባራት እንዲያጠናክሩ ጠይቀው በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ካሉ ተቋማት ጋር ብቁ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትንም አቅም መፍጠር እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት። 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው በአገሪቱ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን ለኅብረተሰቡ በተገቢው መንገድ ለመስጠት ባንኩ የመዋቅር የአሰራር ለውጦችን አድርጓል ብለዋል።


 

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ ባንኩ በመላ አገሪቱ የተገልጋዩን የኅብረተሰብ ክፍል ያገናዘበ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በማቅረብ የተገልጋዮችን ቁጥር ከ6 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ማድረሱን ተናግረዋል።

በዚህም ከተገልጋይ ደንበኞችም ከ107 ቢሊየን ብር በላይ ተቀማጭ መሰብሰቡን ጠቁመው በቀጣይም አገልግሎቱን ለማጠናከር የተጀመሩ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያረጋገጡት።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ኑር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኑሪ ሁሴን በበኩላቸው ባንኩ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የጀመረበትን 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላለፉት ሦስት ወራት በልዩ ልዩ መርኃ ግብሮች ሲያካሄድ መቆየቱን ጠቅሰዋል። 


 

በእነዚህ ዝግጅቶች ኅብረተሰቡ ስለ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ያለውን ግንዛቤ እንዲያጎለብትና አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉን ጠቅሰው አገልግሎቱን ለማጠናከር የሚያስችል በርካታ ጠቃሚ ውይይቶች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።  

በመርኃ ግብሩ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ ውጤታማ እንዲሆን የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ ግለሰቦች ብሎም ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች እውቅናና ሽልማት አበርክቷል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም