ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የተጀመረውን ጥረት በሙሉ አቅማችን እንደግፋለን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የተጀመረውን ጥረት በሙሉ አቅማችን እንደግፋለን
አሶሳ ፤ የካቲት 16 / 2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችውን ጥረት በሙሉ አቅማችን እንደግፋለን ሲሉ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በባህር በር ጉዳይ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ የተገኙ ተሳታፊዎች ገለጹ።
በዓለም ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የባህር በር ከሌላቸው 44 አገራት በህዝብ ቁጥር ኢትዮጵያ አንደኛ ናት።
ኢትዮጵያ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት የባህር በር ባለቤት የነበረች ብትሆንም በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች የባህር በሯን እንድታጣ ተደርጋለች።
የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር ) እና የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ ታህሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ መፈራረማቸው ይታወሳል።
የባህር በር አጠቃቀምን አስመልክቶ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ከተሳተፉት መካከል አቶ አብዱልማሙድ ኢብራሂም በሰጡት አስተያየት፤ ለኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ የህዝቦቿ የዘመናት ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት የአገሪቱን የባህር በር የማግኘት እንቅስቃሴ የማይደግፍ ይኖራል ብዬ አላምንም ያሉት አስተያየት ሰጪው ፤ ለአፈጻጸሙ የማንከፍለው መስዋእትነት የለም ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ አጠይብ ሙስጣፋ የተባሉ ሌላው ተሳታፊ፤ የባህር በር ማጣት በኢኮኖሚ ምን ያህል እንደጎዳን እየጨመረ ከመጣው የኑሮ ውድነት መረዳት ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መረጋጋት ለአፍሪካ መረጋጋት ወሳኝ ነው ያሉት ተሳታፊው፤የአገሪቱ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ሰጥቶ በመቀበል ለጋራ ተጠቃሚነት የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ማድረጓ ኢንቨስትመንትን የመሳብ አቅሟ ከፍተኛ እንደሚሆን የተናገሩት ደግሞ አቶ አዲሱ አስኔ ናቸው።
ተለዋዋጭ በሆነው የአለም ፖለቲካ የባህር በርን ጉዳይ ለነገ ሳይባል በመንግስት ትኩረት መሰጠቱ ተገቢና የሚደነቅ አካሄድ እንደሆነ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ በመንግስት የተጀመረው ጥረት የተሳካ እንዲሆን አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
ለዚህ ደግሞ የውስጥ አንድነትን በሚገባ በማጠናከርና ብሄራዊ ስሜትን ማጎልበት የሁላችንም ሃላፊነት ይሆናል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
"የባህር በር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እና ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ወደብ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ዛሬ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል።
በመድረኩም የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።