ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በድሬዳዋ ከተማ በሚከናወነው የ''ድሬ ሲቲ ካፕ'' የእግር ኳስ ውድድር ላይ ይሳተፋል

ድሬደዋ ፤ የካቲት 16 /2016(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በድሬደዋ ስታዲየም በነገው ዕለት በ ''ድሬ ሲቲ ካፕ'' የሚያከናውነውን የእግር ኳስ  ጨዋታ ምክንያት በማድረግ ድሬዳዋ ከተማ ገብቷል።

"ድሬ ሲቲ ካፕ" በሚል መሪ ሃሳብ በድሬደዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም በሚካሄደው ውድድር ላይ ለመሳተፍ ብሔራዊ ቡድኑ በትናንትናው ዕለት ድሬደዋ ከተማ ገብቷል። 

በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የተመራው ብሔራዊ ቡድን ድሬደዋ አየር ማረፊያ ሲደርስ የድሬደዋ አስተዳደር የስፖርት ዘርፍ አመራሮች ደማቅ  አቀባበል አድርገውለታል። 

የድሬደዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ፊራኦል ቡልቻ እንደተናገሩት፤ ብሔራዊ ቡድኑ ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በተደረገና የሰው ሰራሽ የሳር ንጣፍ በለበሰው ሜዳ ላይ የመጀመሪያውን ጨዋታ የሚያደርግ በመሆኑ ኩራት ይሰማናል ብለዋል። 

ቡድኑ በደጋፊው ፊት ከኡጋንዳ አቻው ጋር የሚያደርገው ጨዋታ አስደሳችና ለተተኪ የድሬደዋ ተጫዋቾች መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል። 

በቅርቡ የሰው ሰራሽ ሳር ንጣፍ የተደረገለት የድሬደዋ ስታዲዮም በፊፋ ቴክኒካል ቡድን የሜዳውን ጥራትና ደረጃ መመርመሩ የሚታወስ ሲሆን ቴክኒካል ቡድኑም የመጨረሻውን ውጤት በቅርቡ ያሳውቃል ተብሎም እየተጠበቀ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም