ተመራቂዎች ያስተማራቸውን ማህበረስብ በታማኝነትና በቁርጠኝነት ሊያገለግሉ ይገባል- ወለጋ ዩኒቨርሲቲ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂዎች ያስተማራቸውን ማህበረስብ በታማኝነትና በቁርጠኝነት ሊያገለግሉ ይገባል- ወለጋ ዩኒቨርሲቲ
ወለጋ፤ የካቲት 16/ 2016 (ኢዜአ)፦ተመራቂዎች በትምህርት ወቅት ያሳዩት ትጋትና ልፋት ውጤት የሚኖረው ያስተማራቸውን ማህበረሰብ በታማኝነትና በቁርጠኝነት ሲያገለግሉ እንደሆነ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ዩሱፍ ገለፁ።
የወለጋ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 1374 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን የሱፍ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ ተመራቂዎች በትምህርት ወቅት ያሳዩት ትጋትና ልፋት ትርጉም የሚኖረው ያስተማራቸውን ማህበረሰብ በታማኝነት እና በቁርጠኝነት ሲያገለግሉ ነው።
ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንቱ ''ተመራቂዎች ከዚህ ግቢ ስትወጡ ሰፊ ስራ ይጠብቃችኋል፤ አገራችሁን አለም የደረሰበት የስልጣኔ ማማ ላይ ለማድረስ ልትሰሩ ይገባል'' ብለዋል።
የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ እና የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል አቶ ምስጋኑ ቱሉ በበኩላቸው ሀገራችን የጀመረችውን የለውጥ ጎዳና አስፍታ እንድትቀጥል የተማረ የሰው ሀይል ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
''ሀገራችንን ስናገለግልም አዳዲስ ተፅእኖ ፈጣሪ ታሪኮችን በመስራት ሊሆን ይገባል እንጂ ተቀጣሪ ሆናችሁ ለመኖር ሊሆን አይገባም'' ብለዋል።
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ዲፓርትመንት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መልካ ሂካ ዩኒቨርሲቲው ለ18ኛ ጊዜ ማስመረቁን ገልፀዋል።
በመንፈቅ አመቱ ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል 234ቱ በመጀመሪያ ዲግሪ 422ቱ በሁለተኛ ዲግሪ ዘጠኝ ተማሪዎችን ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ ማስመረቁ ተገልጿል።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው የመውጫ ፈተና ለሁለተኛ ዙር ተፈትነው ያለፉ 709 ተማሪዎችን አስመርቋል።
በተመሳሳይም የመቱ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ተወካይ ፕሬዚዳንትና የአካዳሚክ ጉዳዮች ዲን እንዲሁም የጥናትና ምርምርና ማኅበረሰብ ግንኙነት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር በድሉ ተካ ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂዎች ወደ ስራው ዓለም ሲቀላቀሉ አገልጋይነትን በታማኝነት፣ ፈተናዎችን በትዕግስት በማለፍ ሀገር የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በቀሰሙት ዕውቀትና ባገኙት ክህሎትም የአካባቢያቸውን ሀብት ወደ ጥቅም በመቀየር በሀገር ልማትና ብልፅግናን የማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ አባልና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸው ሀገሪቱ ያላትን እምቅ ሀብት በስራ ላይ በማዋል በሀገር ዕድገት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በሀገር ወዳድነት መንፈስ እንዲወጡ ተመራቂዎችን ጠይቀዋል።
በታታሪነትና በታማኝነት በመስራት የወል እሴቶቻችንንና የጋራ ሀብቶቻችንን በወል በመጠቀምም የአምራችነትና ሀገር የማልማትና ዕድገቷን የማረጋገጥ ተልዕኮዎችንም እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው በጤና ሳይንስ፣ በቢዝነስና በኢኮኖሚክስ እንዲሁም በሌሎች ኮሌጆቹ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች 297 ወንዶችንና 182 ሴቶችን በድምሩ 479 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ድግሪ እንዲሁም 133 ወንዶችንና 19 ሴቶችን 152 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ ማስመረቁም ታውቋል።
መቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ የዛሬው ለአስረኛ ዙር ሲሆን እስካሁን ከ27 ሺ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች በአንደኛና በሁለተኛ ዲግሪ ማስመረቁን የዩኒቨርሲቲው ሬጂስትራር ክፍል መረጃ ያመለክታል።