ቀጥታ፡

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለሲዳማ ክልል የደህንነት ካሜራዎች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለሲዳማ ክልል የፀጥታ ተቋማትን ለማጠናከር የሚያገለግሉ የደህንነት ካሜራዎች ድጋፍ አደረገ፡፡

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ አቅምን የተላበሱት የደህንነት ካሜራዎቹ ግምታዊ ዋጋቸው 25 ሚሊዮን ብር መሆኑን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመለክታል።

ካሜራዎቹ የሐዋሳ ከተማን እንዲሁም የክልሉን ፖሊስ አሰራር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማዘመን የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው በርክክቡ ወቅት ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ደሳለኝ ለሲዳማ ክልል የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ካሜራዎቹን እና ተያያዥ የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶችን አስረክበዋል።


 

በርክክቡ ወቅትም አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ባስተላለፉት መልዕክት ኢንስቲትዩቱ ለክልሉ መንግሥት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የተረከቧቸው ቴክኖሎጂዎች ክልሉን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ላይ የሚኖራቸው ሚና ጉልህ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም