ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የሀገር ባለውለታ ተቋም ነው-አቶ ቀጀላ መርዳሳ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የምድረ ቀደምቷን ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባሕል፣ ቅርስ በመሰነድና ለትውልድ በማስተላለፍ  የሀገር ባለውለታ ተቋም መሆኑን የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ያስገነባው ባለ 17 ወለል አዲስ ሕንፃ አስመርቋል።


 

የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ፤ በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ከ80 ዓመታት በፊት የተቋቋመው አገልግሎቱ ትልቅ ከፍታ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የባለብዙ ታሪክ፣ ባህል እና ቅርስ ያላት ግን ያልተነገረላት ምድረ ቀደምትና የ13 ወራት ባለፀጋ ሀገር በመሆኗ አገልግሎቱ በዚህ ረገድ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።

አገልግሎቱ ሀገሪቱ ያሏትን መንፈሳዊ፣ ቁሳዊ፣ ባሕላዊና ሀይማኖታዊ ትሩፋቶችን ከትበው፣ ሁነትን መዝግበው፣ ጥበብና ዕውቀትን አስፍረው የያዙ ጽሑፍና የቃል ታሪካዊ ቅርሶች ለማስተላለፍ ትልቅ አበርክቶ አለው።

ሀገሪቱ ያለፈችባቸው ጠመዝማዛ መንገዶችና የተሻለውን ነገ ለማሳየትና ሀገር በቀል እውቀት፣ ጥበብና ሥልጣኔ ለትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚያግዝም  እንዲሁ።


 

አገልግሎቱ በተለያዩ አደረጃጀቶች እና ስያሜዎች የሀገሪቱን የመረጃ ሀብቶች በማደራጀት፣ በመንከባከብና በመጠበቅ፤ለትምህርት ጥናትና ምርምር ሀብቶችን በአንድ ማዕከል ሥር በማሰባሰብና ለትውልድ በመዘከር ትልቅ ለሀገር ውለታ መዋሉንም ገልፀዋል።

ተቋሙ የዕውቀት አስተዳደርን በማጎልበት፣በቴክኖሎጂ ለማዘመን፣ መረጃዎቹን በሳይንሳዊ ዘዴ ለመጠበቅ ፣ በቀላሉ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና ወደ ከፍተኛ ደረጃ በማሸጋገር ከአፍሪካ ቀዳሚ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አንዱ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

አዲሱ ህንፃም የልዩ የመዛግብትና የጽሑፍ ቅርሶች መጠበቂያና ማደራጃ በመሆን ተልዕኮውን ዕውን ለማድረግ እንደሚበጅ ገልፀዋል።

አገልግሎቱን ይበልጥ እንዲስፋፋ፣ ለማህበረሰብ ንባብ መዳበር፣ የፅሁፍ ቅርሶች ጥበቃ፣ እንክብካቤ እና የመረጃ ሀብት በማሰባሰብ ራዕይና ተልዕኮ እንዲሳካ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።


 

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኮኖአምላክ መዝገቡ የህንጻው መመረቅ  ለኢትዮጵያ ትልቅ ታሪካዊ እርምጃ እንደነበር ጠቁመዋል።

ብዙ የተቀበለ፣ ብዙ የሰጠ ተቋም ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ብዙ ወዳጆች ያሉት አንጋፋ ተቋም ነው ብለዋል።


 

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተቋሙ አዲስ ሕንፃ ግንባታ ስኬት እንዲሁም የአገልግሎቱ ባለውለታዎችና ትልቅ አበርክቶ ለነበራቸው ግለሰቦች ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም