ቀጥታ፡

የፓሪስ የኦሎምፒክ ችቦ ቅብብሎሽ ስነ-ስርዓት በሠመራ ከተማ ተካሄደ

ሠመራ፤ የካቲት 16 /2016(ኢዜአ)፡- የፓሪስ የኦሎምፒክ ችቦ ቅብብሎሽ  ስነ-ስርዓት  ዛሬ  በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ ተካሄደ። 

የፓሪስ የኦሎምፒክ ችቦ ቅብብሎሽን ያደረጉት የአፋር ክልል ከኦሮሚያ ክልል ጋር ሲሆን፤ ስነስርዓቱ የተካሄደው "ኢትዮጵያ ትወዳደር ተወዳድራም ታሸንፍ"  በሚል መሪ ሐሳብ  በተዘጋጀው  ስፖርታዊ ውድድር ነው።

ፓሪስ  ለሚካሄደው ኦሎምፒክ በሀገር አቀፍ ደረጃ የችቦ ቅብብሎሽ ስነ-ስርዓት እየተከናወነ መሆኑ ተመልክቷል።

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፈው ሳምንት የተረከበው የአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ዛሬ   የችቦ ቅብብሎሽ ስነ-ስርዓት  አከናውኗል።

የፓሪስ ኦሎምፒክ ችቦ ቅብብሎሽ ስነ-ስርዓት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀውን ውድድር  ያስጀመሩት በአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ አሚና ሴኮ በወቅቱ እንዳሉት፤  ኢትዮጵያ ተወዳድራ እንድታሸንፍ  የሚደረገው አገር አቀፍ እንቅስቃሴ አበረታች ነው።


 

በዚህም ስነ-ስርዓቱ እንደሌላው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ በአፋር ክልልም መካሄዱን ጠቅሰው፤  ስፖርት ለአብሮነት ለአንድነት ለፍቅር የሚያደርገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ለስነ-ስርዓቱ አዘጋጆች ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፀሐፊ  አቶ ዳዊት አሰፋ በበኩላቸው በአፋር ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ የተከናወነው የዕለቱ ስነ-ስርዓት አድናቆታቸውን ገልጸው፤ ይህም ኢትዮጵያ ተወዳድራ ለማሸነፍ የምታደርገው ጥረት ይጠናከራል ብለዋል።

የኦሎምፒክ ችቦውን ለመረከብ በስፍራው የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ተወካይ አቶ ሰለሞን እንዳለ በበኩላቸው፤ ስነ-ሰርዓቱ ከሌሎች  ተሞክሮ በመውሰድ የበለጠ እንድንሰራ ያደርገናል ብለዋል።

ስፖርት ለሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ፣አንድነትና ሰላም የሚያደርገው አስተዋጽኦም  ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።


 

በዕለቱም ታዳጊዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች  የተሳተፉበት የአጭር ርቀት የሩጫ ውድድርና የተለያዩ  የስፖርት እንቅስቃሴዎች ተካሄደዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስና   ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች አባላት ፣የአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኦሎምፒክ ችቦ የአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አቡበከር ኢሴ ለኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ተወካይ ለአቶ ሰለሞን እንዳለ አስረክበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም