ቀጥታ፡

በፓንአፍሪካኒዝም እሳቤ የበለጸገች  አፍሪካን ለመገንባት የአህጉሪቱ ወጣቶች በጋራ ሊሰሩ ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2016(ኢዜአ)፦በፓንአፍሪካኒዝም እሳቤ የበለጸገች  አፍሪካን ለመገንባት የአህጉሪቱ  ወጣት አመራሮች በጋራ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ  ገለጹ።

የአፍሪካ ወጣት አመራሮች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ትናንት ጀምሯል።

ኮንፍረንሱን ያዘጋጁት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር  ናቸው።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ወጣት አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።


 

ወጣቶቹ በኮንፍረንሱ በአመራርነት፣ ዲፕሎማሲና በዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ መርሐ ግብር እንደሚያካሄዱ ተገልጿል::

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የነገዋ አፍሪካ እድል ፈንታ የሚወሰነው አሁን  ላይ  ባሉ ወጣቶች ነው።

በመሆኑም የአፍሪካ ወጣቶች በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ በጋራ የበለፀገች አፍሪካን ለመገንባት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በአህጉሪቷ  የወጣቶችን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ በማረጋገጥ የምንመኛትን አፍሪካ እውን ለማድረግ መስራት ይገባል ብለዋል።

በተለይም በአመራርነት  ላይ ያሉ ወጣቶችን በማበረታታትና ተሳትፏቸውን በማሳደግ አህጉሪቷን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ወጣቶችም የአህጉሪቷን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገቷን ለማፋጠን  ቁርጠኛና ባለራዕይ  በመሆን  መስራት እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስትሯ አክለዋል።


 

የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር  ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጫላ አሰፋ  በበኩላቸው የአፍሪካን እድገት ለማፋጠን   ወጣቱ ትውልድ ያለውን አቅም መጠቀም እንደሚገባው ገልጸዋል።

ለዚህም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊው መስክ  ለጋራ ስኬት ሊሰራ ይገባል ብለዋል::

ኢዜአ ያነጋገራቸው በኮንፍረንሱ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች በበኩላቸው የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ወጣቶች አቅማቸውን በመጠቀም በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ከኬንያ የመጣችው ፎይቤ ኦንያንጎ  የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ወጣቱ ከምቹ መደላድልና ከባቢ ብቻ ከመፈለግ  ወጥቶ ትርጉም ያለው  ስራ መስራት ይገባዋል ብላለች።

ከደቡብ ሱዳን የመጣችው ኩዌር ፒተር ዳንግ በበኩሏ ለአፍሪካ የላቀ እድገት ወጣቶች  በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብላለች።

ኢትዮጵያዊቷ ቅድስት ኤፍሬም በበኩሏ ወጣቱ ያለውን እምቅ አቅም ተጠቅሞ የአፍሪካን የነገን ተስፋ ማለምለም ይገባዋል ብላለች።

ወጣቶቹ በሶስት ቀናት የአዲስ አበባ ቆይታቸው የአድዋ መታሰቢያ ጨምሮ በከተማዋ የተገነቡ የተለያዩ ፓርኮችን እንደሚጎበኙም ተጠቁሟል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም