የመጀመሪያው የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንት ከየካቲት 18 እስከ የካቲት 22 ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንት ከየካቲት 18 እስከ የካቲት 22 ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2016(ኢዜአ)፦የመጀመሪያው የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንት ከየካቲት 18 እስከ የካቲት 22 እንደሚካሄድ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጠው መግለጫ የመጀመሪያው የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንት "የጋራ ጥረታችን ለዲጂታል ኢትዮጵያችን" በሚል መሪ ሀሳብ በሃገር አቀፍ ደረጃ እንደሚካሄድ አስታውቋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ (ዶ/ር) በአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ውስጥ ቴክኖሎጂ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት ለማስቻል እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በመሆኑም የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ንቅናቄ በመፍጠር የህብረተሰቡን ቴክኖሎጂ የመጠቀም ባህል በማሳደግ በልማትና ምጣኔ ሀብት ላይ ያለውን አስተዋጽኦ ከፍ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ የዲጂታል ሳምንት ለማህበረሰቡ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስራዎች ለማስተዋወቅ፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም ግንዛቤን ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል።
ሳምንቱ መንግስት የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለልማትና ምጣኔ ሀብት ዕድገት በማዋል የማህበረሰቡን የዕለት ከእለት እንቅስቃሴ ቀላል እና ቀልጣፋ ለማድረግ እያከናወናቸው ያሉ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን የሚያሳይበት እንደሆነ ተገልጿል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንት የፓናል ውይይቶች፣ ጉብኝቶችና ሌሎች በዘርፋ ግንዛቤ የሚፈጥሩ ሁነቶች የሚከናወኑ ሲሆን የዘርፉ የክልል ሀላፊዎችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ተነግሯል።