ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ- መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ባለ 17 ወለል አዲስ ሕንፃ ዛሬ ያስመርቃል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2016(ኢዜአ)፦የ80 ዓመታት ዕድሜ ባለፀጋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ባለ 17 ወለል አዲስ ሕንፃ ዛሬ ያስመርቃል።

የ80 ዓመታት ዕድሜ ባለፀጋው የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ባለ17 ወለል አዲስ የቤተ መዛግብት ሕንፃ ዛሬ ያስመርቃል።

በ1936 ዓ.ም "የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር" በሚል ስያሜ በቀዳሚዊ አፄ ኃይለሥላሴ የተቋቋመው ይህ ተቋም የተለያዩ ስያሜዎች ነበሩት።

ለአብነትም በ1958 ዓ.ም "ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት"፣ በ1972 "ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት መምሪያ"፤ በ1986 "የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት ድርጅት" የሚል ስያሜ የነበረው ሲሆን አሁን ላይ "የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት" የሚል ስያሜ ይዟል።

በኢትዮጵያ ታሪክ የመዛግብት፣ የመፃሕፍት እና ቅርሶች ክምችቱ ግንባር ቀደም የሆነው አገልግሎቱ፣ በ80 ዓመታት ውስጥ የአይነተ ብዙ ፅሁፍ፣ የድምፅና የምስል ቅጂዎችን ይዟል።

አገልግሎቱ በውስጡ አምስት ቤተ መጻሕፍትን ያቀፈው ሲሆን የንባብ፣ የማጣቀሻ፣ የውሰትና ሌሎችም አገልግሎት ይሰጣል።

የኢትዮጵያን ትናንት ለመጭው ትውልድ የሚዘክሩ ከመላ ሀገሪቱ ተቋማትና ግለሰቦች የተሰባሰቡ ሀገራዊ ሰነዶች፣ የሸክላ ሙዚቃዎች፣ ድርሳናት፣ የብራና እና ጥራዝ መፃሕፍትና ሌሎች ሰነዶችንም አቅፏል።

በዓለም አቀፉ የሳይንስ የትምህርትና የባሕል ድርጅት/ዩኔስኮ የተመዘገቡ 12 የፅሁፍ ቅርሶችን ባለቤት ተቋም ነው።

በቤተ መዛግብት ክምችት ረገድ በአፍሪካ ምርጥ አምስት ቤተ መዛግብት መካከል አንዱ ለመሆን እየሰራ ያለው አገልግሎቱ፣ ዛሬ በማስመረቅ ላይ የሚገኘው ሕንፃም ለዘመናት የነበረበትን የቦታ ጥበት እንደሚቀርፍ ታምኖበታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም