ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን የሚመጥን የሜካናይዝድ ኃይል እየተገነባ ነው - የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን የሚመጥን የሜካናይዝድ ኃይል እየተገነባ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።

የሜካናይዝድን የግዳጅ አፈፃፀም ብቃት ለማሳደግ በተዘጋጀ ጥናት ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ተካሂዷል።

በውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሜካናይዝድ ኃይሉ ራሱን ችሎም ይሁን ከእግረኛው ሰራዊት ጋር በርካታ ግዳጆችን መፈፀሙን አውስተዋል።

አሁን ላይ እንደሀገር ካለው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ በቀጣይ ሊኖር ከሚችል ግዳጅና ነገን ታሳቢ ያደረገ ሜካናይዝድ እየተገነባ መሆኑንም ገልፀዋል።


 

ጀኔራል መኮንኖችና ከሁሉም የሜካናይዝድ ክፍሎች የተውጣጡ አመራሮች በውይይቱ መሳተፋቸውንና እንደተቋም የተዘጋጀው ጥናት ለቀጣይ ግዳጅ አፈፃፀም የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

የተዘጋጀውን ጥናታዊ ፅሑፍ የመከላከያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል ይታያል ገላው ማቅረባቸውንና በጥናቱ መሠረት በሰው ኃይል ሜካናይዝድ ክፍሎቹ ላይ የሚኖረውን አወቃቀር በተመለከተ ገለፃ ማድረጋቸውን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም