የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የከተማዋን የመንገድ ሽፋንና ዘመናዊነት ለማሻሻል የሚረዳ ውሳኔ አሳለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የከተማዋን የመንገድ ሽፋንና ዘመናዊነት ለማሻሻል የሚረዳ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የከተማዋን የመንገድ ሽፋንና ዘመናዊነት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰት ሊያሳድግ የሚችል የመንገድ ኮሪደር ልማቶች ላይ እና የአካባቢ ልማቶች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በዛሬው እለት 3ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል።
ካቢኔው አዲስ አበባ የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ የሚመጥን የመንገድ ልማት ኮሪደሮችን ለመገንባት የሚያስችል እቅድ ላይ የተወያየ ሲሆን የከተማዋን አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን እና ዘመናዊነት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰት ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሳድግ የሚችል የመንገድ ኮሪደር ልማቶች ላይ እና የአካባቢ ልማቶች ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህ መሠረት የሚለሙት የመንገድ ኮሪደሮች የሚከተሉት ይሆናሉ:-
ከአራት ኪሎ በመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ድልድይ (7 ኪ.ሜትር)
ከቦሌ አየር መንገድ እስከ መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ (4.9 ኪ.ሜትር)
ከመገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ በአራት ኪሎ በኩል የአድዋ ድል መታሰቢያ አካባቢ ድረስ (6.4 ኪ.ሜትር)
ከፒያሳ አድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ፣ በለገሃር ሜክሲኮ፣ በሳርቤት በኩል እስከ ወሎሰፈር (10 ኪ.ሜትር) ናቸው።
እነዚህ የመንገድ ኮሪደር ልማቶች ሁለንተናዊ የመንገድ ዘመናዊነት ያሟሉ ከመሆናቸውም በላይ ዓለም አቀፍ የስማርት ሲቲ ስታንዳርድን በማሟላት የከተማዋን ገጽታ የሚያሻሽሉ መሆናቸው ተገልጿል።
የመንገድ ኮሪደር ፕሮጀክቶቹ አዋሳኝ የወንዝ ተፋሰሶችን ያቀፉ፣ የሳይክልና ሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ የከተማዋን ማስተር ፕላን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተጨማሪም አስፈላጊ በሆኑ የኮሪደሩ ቦታዎች ላይ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ ተሸጋጋሪ ድልድዮች፣ ማሳለጫዎች እና ሰፋፊ መጋቢ መንገዶችን ያቀፈ ሲሆን የከተማ አረንጓዴ ልማትን ያካተተ እንደሚሆንም ታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔም የቀረበውን የመንገድ ኮሪደር ልማት እቅድ በጥልቀት መርምሮ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን ከነገው እለት ጀምሮ ወደ ስራ እንዲገባና ልዩ ክትትል እንዲደረግለት ወስኗል።