ቀጥታ፡

የአፍሪካ ወጣት አመራሮች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2016 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ወጣት አመራሮች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።

ኮንፍረንሱን ያዘጋጁት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር ናቸው።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ከ200 በላይ ወጣት አመራሮች ታድመዋል::

ወጣቶቹ ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት በአመራርነት፤ ዲፕሎማሲና በዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ መርሃ-ግብር እንደሚያካሄዱ ተገልጿል::

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የነገዋ አፍሪካ እድል ፈንታ የሚወሰነው አሁን ላይ ባሉ ወጣቶች እንደሆነ ጠቁመዋል::

በመሆኑም የአፍሪካ ወጣቶች በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ በጋራ የበለፀገች አፍሪካን ለመገንባት ሊሰሩ ይገባል አስረድተዋል::

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በአህጉሪቷ የወጣቶችን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ በማረጋገጥ የምንመኛትን አፍሪካ እውን ለማድረግ መስራት ይገባል ብለዋል::

በተለይም በአመራርነት ላይ ያሉ ወጣቶችን በማበረታታትና ተሳትፎአቸውን በማሳደግ አህጉሪቷን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ ተናግረዋል::

የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጫላ አሰፋ በበኩላቸው የአፍሪካን እድገት ለማፋጠን ወጣቱ ትውልድ ያለውን አቅም መጠቀም እንደሚገባው አንስተዋል።

ለዚህም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊው መስክ ለጋራ ስኬት ሊሰራ ይገባል ብለዋል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም