አንጋፋው ሙዚቀኛ ጌታቸው ካሳ ለሙያውና ለሀገር ክብር በተግባር ሃውልት አቁሞ ያለፈ ሙያተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አንጋፋው ሙዚቀኛ ጌታቸው ካሳ ለሙያውና ለሀገር ክብር በተግባር ሃውልት አቁሞ ያለፈ ሙያተኛ ነው
አዲስ አበባ፤የካቲት 15/2016 (ኢዜአ)፡- አንጋፋው ሙዚቀኛ ጌታቸው ካሳ ለሙያውና ለሀገር ክብር በተግባር ሃውልት አቁሞ ያለፈ ሙያተኛ መሆኑን የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰርፀ ፍሬስብሃት ገለጹ፡፡
በዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ሥራዎቹ የሚታወቀው የድምጻዊ ጌታቸው ካሳ ሥርዓተ-ቀብር በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዛሬ ተፈጽሟል።
የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰርፀ ፍሬስብሃት በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አንጋፋው ሙዚቀኛ ጌታቸው ካሳ ግማሽ ምዕተ-ዓመትን በተሻገረው የሙዚቃ ሥራው ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎችን ለአድማጮቾች አበርክቷል።
ከእነዚህ የሙዚቃ ሥራዎቹ መካከል አገሬን አትንኳት፣ አዲስ አበባ፣ አትጥፋ ከጎኔ፣ ብርቱካን ነሽ ሎሚ እና ትዝታ የተሰኙ ይገኙበታል ብሏል።
ድምጻዊ ጌታቸው የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወደ ዘመናዊ ካሸጋገሩ ባለሙያዎች አንዱ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በስራዎቹም ለሀገሩንና ለሙያው ያለውን ክብር አሳይቶ አልፏል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበራት ህብረት ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩ በበኩሉ ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ አገሩን የሚወድ ሁለገብ የሙዚቃ ባለሙያ ነው ብሏል።
ድምጻዊ ጌታቸው በሙዚቃ ሕይወቱ አገር ከፍ ሲያደርግ የኖረ፤ ትውልድ ያስተሳሰረ መሆኑንም ጠቅሷል።
በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ የአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች፣ የሙያ አጋሮቹ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሙያ አድናቂዎቹ ተገኝተዋል።