ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተደረገው የመግባቢያ ሥምምነት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውና የጋራ ልማትን የሚያፋጥን ነው - አምባሳደር ደግፌ ቡላ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የተደረገው የመግባቢያ ሥምምነት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው፣ ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክርና የጋራ ልማትን የሚያፋጥን መሆኑን የፌደራል ፍትህና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ገለጹ።

በፌደራል ፍትህና ሕግ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀው በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ዓለም አቀፍ ህጋዊነት እና አንድምታ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።


 

የውይይቱ ዓላማም በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል የተደረገው ስምምነት ያለውን አንድምታ በተመለከተ ግንዛቤ ማስጨበጥ መሆኑ ተገልጿል።

በመድረኩ በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ዓለም አቀፍ ህጋዊነት እና አንድምታ ላይ ያተኮረ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የፌደራል ፍትህና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት  ኢንስቲትዩቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የሀገርን ጥቅም በሚያስከብሩ ጉዳዮች ላይ ጥናት እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ እየሰጠ ይገኛል።

በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ዓለም አቀፍ ህጋዊነትና አንድምታ ላይ ያተኮረው የውይይት መድረክም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ትልቅ ህዝብ ይዛ ለአመታት የባህር በር ሳይኖራት መቆየቷን ገልጸው የባህር በር የኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በጋራ የመልማት መርህን በማስቀደም የባህር በርና ወደብ የማግኘትና የመጠቀም ፍላጎትም መብትም እንዳላት ጠቁመዋል።

በዚህም በቅርቡ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እና ህጋዊ መሰረት ያለው መሆኑን አመላክተዋል።

ስምምነቱ ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክርና የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን አንስተዋል። 

በዚህ ዙርያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነሱ አሉታዊ ምልከታዎች ኢትዮጵያ እጇን አጣጥፋ እንድትቀመጥና እንዳትለማ የሚፈልጉ አካላት የሚያንጸባርቋቸው መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ለሌሎች ሀገራት ሰላምና ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተች መሆኗን ጠቅሰው በጋራ ለመልማት የምታደርገው ጥረትም የማንንም መብት የሚጋፋ አለመሆኑን አመላክተዋል።

በመገናኛ ብዙሀን እንዲሁም በዲፕሎማሲው መስክ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች መልካም መሆናቸውን በመግለጽ መሰል ተግባራትን በተለያዩ አማራጮችና ቋንቋዎች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።


 

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ስምምነቱ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎላና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑን አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም