ቀጥታ፡

የህዝብን አንድነት የሚያጠናክር የጋራ ትርክት ለመገንባት የኪነ-ጥበብን አቅም በአግባቡ መጠቀም ይገባል - አቶ ሞገስ ባልቻ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2016(ኢዜአ)፦ የህዝብን አንድነት የሚያጠናክር የጋራ ትርክት ለመገንባት የኪነ-ጥበብን ሃያል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ተናገሩ።

የአዲስ አባበ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ “ኢትዮጵያዊነት የሥነ-ጥበብ ምናብ ሠረገላ፣ የወል ትርክት አለላ” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው 15ኛው ከተማ አቀፍ የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ዛሬ ተከፍቷል።

በግዮን ሆቴል ለሕዝብ ዕይታ ክፍት የተደረገው ፌስቲቫል ለሦስት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ እንደገለጹት የሚያግባባ ብሔራዊ ትርክትን ለማሳደግ ኪነ-ጥበብ ከፍተኛ አቅም አለው።


 

የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርጎ በማሳየት ትልቅ ሚና እንደነበረው አስታውሰው ይህንን አቅም የህዝብን አንድነት የሚያጠናክር የጋራ ትርክት ለመገንባት መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

ዛሬ የተከፈተው ፌስቲቫል የኢትዮጵያን የኪነ-ጥበብ ሀብቶችን አጉልቶ ለማሳየትና የእርስ በእርስ ትስስርን ለማጠናከር ትልቅ እገዛ እንዳለውም ነው ያብራሩት።

የጥበብ ሥራ ለማኅበራዊና ለሀገራዊ ፋይዳ ሲባል በጥንቃቄ ሊሰራ እንደሚገባም አቶ ሞገስ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው አንጋፋ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሀገርን አርማ ተሸክመው የዐርበኝነት ገድል መፈጸማቸውንም አንስተዋል።


 

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሒሩት ካሣው (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያዊነትን ለማጽናት፣ ለማነጽ እና ወደሚፈለገው ልዕልና ለመሻገር የኪነ-ጥበብ ሚና አይተኬ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገርን ለዑላዊነት አስከብሮ ዓለም አቀፋዊነትን ለማስፈን ኪነ-ጥበብ ወሳኝ መሆኑንም ጨምረው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዕልናውንና ሕብረብሔራዊነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያዊነት እንዲጸና የባህል፣ የኪነጥበብና የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን መሠረተ ልማቶች እየተዘረጉ መሆናቸውን ዶክተር ሂሩት ገልጸዋል።

አዲስ አበባ የኪነ-ጥበብ ማዕከል በመሆኗ የቱሪስት ፍሰትና ቆይታን ለመጨመር የኪነ-ጥበብ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፌስቲቫሉ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ፌስቲቫሉ ከዛሬ የካቲት 15 እስከ 17 ለሦስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶች ይቀርቡበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም