በክልሉ የጤና ተቋማትን አገልግሎት የሚያጠናክሩ የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጤና ተቋማትን አገልግሎት የሚያጠናክሩ የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ
ባህር ዳር፤ የካቲት 15/2016 (ኢዜአ) ፦በአማራ ክልል የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር የሚያግዙ 25 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ እንደገለጹት፣ ድጋፉ በክልሉ የሚስተዋለውን የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ለማቃለል ያግዛል።
በድጋፍ ከተሰጡ የሕክምና ቁሶች መካከል 16 የሰመመን መስጫ እና 15 የአልትራሳውንድ መሳሪያዎች እንዲሁም ለምርመራ የሚውሉ አልጋዎች ይገኙበታል።
ከእዚህ በተጨማሪ ለእናቶችና ልጃገረዶች ስነ-ተዋልዶ እንዲሁም ለጨቅላ ሕጻናት ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ የሕክምና ቁሶችና መድኃኒቶች ድጋፉ መደረጋቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።
የሕክምና መሳሪያዎቹና መድሀኒቱ ቀደም ሲል በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ደርሶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ለሚገኙ የጤና ተቋማት እንደሚሰራጩም ገልፀዋል።
አቶ አብዱልከሪም እንዳሉት ድጋፉ በተለይ በዚህ ዓመት በጤና ጣቢያ ደረጃ ለተጀመረው የእናቶች ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው።
ድጋፉ በተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ መደረጉን የገለጹት ኃላፊው፣በክልሉ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል እየተሰራ በመሆኑ ድጋፉ በቀጣይም እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
በተባበሩት መንግስታት የስነህዝብ ፈንድ የኢትዮጵያ ሰብአዊ ጉዳዮች ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ጀምስ ዋንያማ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በክልሉ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል በሚሰሩ ሥራዎች የራሱን እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
በተለይ የእናቶችን ጤና ለማሻሻል እና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በሚሰሩ ሥራዎችና በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ሲደግፍ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ዛሬም በክልሉ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል የሚያገለግሉ የተለያዩ የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
የተጀመሩ ድጋፎች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ዶክተር ጀምስ አረጋግጠዋል።
በአማራ ክልል በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን የሕክምና ተቋማት መልሶ በማደራጀት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።