ቀጥታ፡

አድዋ የአሸናፊነት ስነ-ልቦናን የገነባና የሀገር ፍቅርን ያጠናከረ ትልቅ ድል ነው -ዶክተር አብዱልአዚዝ ዳውድ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2016 (ኢዜአ)፡- አድዋ የኢትዮጵያውያንን የአሸናፊነት ስነ-ልቦና የገነባና የሀገር ፍቅርን ያጠናከረ ትልቅ ድል ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብዱልአዚዝ ዳውድ ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በሚዘጋጀው በ36ኛው የጉሚ በለል የውይይት መድረክ ላይ ‘’የአድዋ ድል ለወል ትርክት ግንባታ’’ በሚል መሪ ሀሳብ የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት ውይይት ተደርጓል።


 

በዚሁ ጊዜ የክልሉ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብዱልአዚዝ ዳውድ፣ "አድዋ በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በጥቁር ህዝቦች ዘንድ ትልቅ ስፍራ ያለው ድል ነው ብለዋል።

ይህ ትልቅ ድል ኢትዮጵያውያን በጋራ ትግልና በህብረት ባደረጉት ተጋድሎ የተገኘ በመሆኑ የአድዋ ድልን ለጋራ ትርክት ግንባታ ማዋል ይገባል ነው ያሉት።

''ነጠላ ትርክት በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን ሀገር መገንባት አያስችልም'' ያሉት ዶክተር አብዱልአዚዝ፤ የክልሉ ህዝብም አድዋን የመሰሉ የጋራ ትርክቶችን በማጉላት የሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ በንቃት መሳተፍ አለበት ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ በበኩላቸው የአድዋ ድል አንድነትና የኢትዮጵያውን ህብረት የታየበት ታላቅ ድል መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህ ድል ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብም የራሱን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ህዝብ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሃይሉ፤ ድሉ የተሻለች ሀገር ለመገንባት አብሮ መቆምና መደጋገፍን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የዛሬ ትውልድም ይህን ታላቅና በህዝብ አብሮነት የተገኘውን ድል የተሻለች ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሊጠቀምበት እንደሚገባ አስረድተዋል።

በመድረኩ ላይ ''የጋራ ትርክት ግንባታ'' በሚል መሪ ሀሳብ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ሽመልስ ሃይሉ፣ የአድዋ ድል እንደ ሀገር የጋራ ትርክት እንዲኖረን ትልቅ ሚና የሚጫወት ድል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአድዋ ድልን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያውያንን ዘመን ተሻጋሪ አንድነትና ህብረት የሚያጎሉ ክስተቶችና ክንውኖች ለጋራ ትርክት ግንባታ መጠቀምም አስፈላጊ መሆኑን በማውሳት። 

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን አንድነትና ህብረት ለዓለም የታየበት ትልቅ ድል መሆኑን አንስተዋል።

ድሉ የተገኘው በሁሉም አቅጣጫ ያሉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት ተነስተው በመፋለም መሆኑን አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም