የድምጻዊ ጌታቸው ካሳ የስንብት መርኃ ግብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2016(ኢዜአ)፦በዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ሥራዎቹ የሚታወቀው ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ የስንብት መርኃ ግብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ተካሄደ።  

የስንብት መርኃ ግብሩን የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበራት ኅብረት ጋር በጋራ በመሆን ነው ያዘጋጀው።  

በስንብት መርኃ ግብሩ የአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች፣ የሙያ አጋሮቹ፣የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሙያ አድናቂዎቹ ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰርፀ ፍሬስበሃት በዚሁ ጊዜ እንደገለጸው፤ ግማሽ ምዕተ ዓመትን በተሻገረው የሙዚቃ ሥራው ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎችን ለአድማጮች አበርክቷል።  

ከእነዚህ የሙዚቃ ሥራዎቹ መካከል ‘አገሬን አትንኳት’፣ ‘አዲስ አበባ’፣ "አትጥፋ ከጎኔ"፣ “ብርቱካን ነሽ ሎሚ”  እና ‘ትዝታ’ የተሰኙ ይገኙበታል ብሏል።  

ድምጻዊ ጌታቸው የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወደ ዘመናዊ ካሸጋገሩ ባለሙያዎች አንዱ መሆኑንም ጠቅሷል። 

የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበራት ኅብረት ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩ በበኩሉ ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ አገሩን የሚወድ ሁለገብ የሙዚቃ ባለሙያ ነው ብሏል።  

ድምጻዊ ጌታቸው በሙዚቃ ሕይወቱ አገር ከፍ ሲያደርግ የኖረ፤ ትውልድ ያስተሳሰረ መሆኑንም ጠቅሷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም