ከዓድዋ ድል የአንድነት ታሪክ በመማር ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና የብልጽግና ጉዞ ስኬት ጠንክረን እንሰራለን - ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ከዓድዋ ድል የአንድነት ታሪክ በመማር ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና የብልጽግና ጉዞ ስኬት ጠንክረን እንሰራለን - ወጣቶች
ሀዋሳ፤ የካቲት 15/2016(ኢዜአ)፦ ከዓድዋ ድል የአንድነት ታሪክ በመማር ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና የብልጽግና ጉዞ ስኬት ጠንክረን እንሰራለን ሲሉ የሀዋሳ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ድሉንና ጀግኖችን ይበልጥ ያከበረ መሆኑንም ወጣቶቹ አመልክተዋል።
ወጣቶቹ እንደ ጀግኖች አባቶች ሀገርን በማስቀደምና ለልማት ተግቶ በመስራት ኢትዮጵያን በጋራ የማጽናት ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማዋ ወጣቶች መካከል ወጣት ኃይለየሱስ ታምራት እንዳለው፣ የዓድዋ ጀግኖች በአንድነት ለሀገራቸው ዋጋ ስለከፈሉ ለድል በቅተዋል።
እኛ ወጣቶች ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነው ወራሪውን የጣልያን ጦር ድል ከመቱበት አኩሪ ታሪክ በመማር ሀገርን በልማት የማበልጸግ ትልቅ ሃላፊነት አለብን ሲል ተናግሯል።
የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን ባለፈ ለአፍሪካውያን ጭምር የነጻነት ምሳሌ መሆኑን ገልጾ፣ ድሉ በተለይ ለዛሬው ትውልድ ታላቅ የኩራት ምንጭ መሆኑን ገልጿል።
የዓድዋን በዓል በሃዋሳ ከተማ በማክበር ጀግኖች አባቶችን በአግባቡ ለመዘከርና ለማስታወስ ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም አክሏል።
የዓድዋ ድል ለሀገር በአንድነት መቆም ለስኬት እንደሚያበቃ በተለይ ለዛሬው ወጣት አስተማሪ መሆኑን ገልጾ፣ ከዓድዋ አባቶችና እናቶች ጀግንነትን ብቻ ሳይሆን አብሮነትን በመማር ኢትዮጵያን በልማት ወደ ፊት ማምጣት ይገባል ነው ያለው።
እንደ ጀግኖች አባቶች ሀገርን አጽንቶ ከነሙሉ ክብሯ ለመጪው ትውልድ ለማቆየት የወጣቱ ሃላፊነት ከፍተኛ መሆኑንም ነው ያመለከተው።
ሌላው የከተማዋ ወጣት በቃሉ መሠረት በበኩሉ፣ የዓድዋ ድል ከሀገር አልፎ ለመላው አፍሪካውያንና ለጥቁር ህዝብ ኩራት መሆኑን ተናግሯል።
ለእኛ ለወጣቶች የይቻላልና የአሸናፊነት ስብዕናን ያጎናፀፈን የኩራታችን ምንጭ የሆነ ድል ነው ብሏል።
በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ የተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ድሉን ይበልጥ ለማጉላትና በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያውያን በጋራ የከፈሉትን የመስዋዕትነት ታሪክ ለሌሎች ለማሳየት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጿል።
ኢትዮጵያውያን ከየአቅጣጫው በመሰባሰብ ለሀገራቸው ክብር በጋራ በከፈሉት መስዋዕትነት በዓድዋ ድል ደማቅ ታሪክ አቆይተውናል ያለው ወጣቱ፤ መታሰቢያው ድሉንና ጀግኖችን ይበልጥ ያከበረና ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተወከሉበት መሆኑን ጠቁሟል።
የዓድዋ ጀግኖች በወቅቱ ከሁሉ በፊት ሀገር ትቅደም በሚል መንፈስ ከየአቅጣጫው ዘምተው የኢትዮጵያን ስምና ክብር ጠብቀው ማቆየታቸውን ተናግሯል።
የዓድዋን ድል መድገም የእኛ ሃላፊነት ነው ያለው ወጣት በቃሉ፣ ትውልዱ ዘወትር ለሀገር ለውጥና እድገት ተግቶ በመስራት ድህነትን ማሸነፍና የጀግኖቹን ታሪክ መድገም እንዳለበት ነው የገለፀው።
የውስጥ እንድነትን በማጠናከር የሀገራችንን ሠላም ለማጽናት እያንዳንዳችን መትጋት አለብን ነው ያለው።
ወጣት ናታኒም ዋሸራ ደግሞ የዓድዋ ተጋድሎ ክብርን ብቻ ሳይሆን አንድነት ለስኬት እንደሚያበቃ ለትውልዱ ትልቅ ትምህርት የሰጠ መሆኑን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታን ብሩህ ለማድረግና ሀገርን አጽንቶ ለማቆየት ሰላም ወሳኝ መሆኑን የተናገረው ወጣት ናታኒም፤ በተለይ ወጣቱ እርስ በእርስ ከሚከፋፍሉ አስተሳሰቦችና ከጥፋት አካላት ራሱን በማራቅ ለሀገሩ ዘብ መሆን እንዳለበት አስገንዝቧል።