ቀጥታ፡

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መገለጫችንም ጉርሳችንም በመሆኑ ሰላምና ደህንነቱን እየጠበቅን ነው - የአካባቢው ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2016(ኢዜአ)፦ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መገለጫችንም ጉርሳችንም በመሆኑ ሰላምና ደህንነቱን በሚገባ እየጠበቅን ነው ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

የጃናሞራ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቄስ መሳፍንት አማረ አካባቢው የተረጋጋና ሰላሙ የተጠበቀ በመሆኑ ጎብኚዎች ይህንን ድንቅ መስህብ እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እ.ኤ.አ በ1978 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበና የጎብኝዎችን ቀልብ ከሚገዙ የመስህብ ስፍራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው።

በአፍሪካ በማራኪ ገፅታቸው ከሚጠቀሱ የተፈጥሮ መስህብ ስፍራዎች በቀዳሚነት የሚነሳው ይህ ፓርክ፥ የዋልያ አይቤክስ፣ የቀይ ቀበሮ፣ የጭላዳ ዝንጀሮና ሌሎችም ብርቅዬ የዱር እንስሳት መገኛ ነው።

እንደ ዝግባ፣ ወይራ፣ ጅብራና ዋንዛ የመሳሰሉ ዛፎችን ጨምሮ በርካታ የብዝሃ ህይወት ሀብትን በውስጡ የያዘው ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 412 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው።


 

የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ፓርኩ መገለጫቸውም ጉርሳቸውም ነው።

የአከባቢው ነዋሪ የሆኑት መምህር ፈንታ ታዬ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከአካባቢው አልፎ የአገር ውድ ሀብት በመሆኑ ህዝቡ ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ እያደረገለት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ወጣት ወርቅነህ ሹምዬ በበኩሉ ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም ማህበረሰብ ከመንግስት ጋር በመሆን የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

የሀገር ሀብት የሆነው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑንና ለጎብኝዎች ምንም ዓይነት ስጋት እንደሌለም ጠቁሟል።


 

በዩኔስኮ በተመዘገበው ፓርክ ውስጥ የሰርጎ ገብ እንቅስቃሴ እንዳይኖር እንደማህበረሰብ በመደራጀት ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ መብራቱ መንገሻ ናቸው።

ቄስ ተሾመ አዘንጌ በበኩላቸው አካባቢያቸው ሌላው ዓለም ያልታደለውን ጸጋ የያዘና ብርቅዬ የዱር እንስሳት የሚገኙበት መሆኑን ገልጸው፥ ወደ ፓርኩ የሚመጡ ጎብኝዎች አካባቢው ፍጹም ሰላማዊ መሆኑን ማወቅ አለባቸው ብለዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብም ጎብኝዎችን እንደቤተሰብ ተቀብሎ በምቾት እንደሚያስተናግዳቸውም አንስተዋል።

ነዋሪዎቹ አክለውም ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ በሰሜን ጎንደር ዞን ያለውን መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎችም አካባቢዎች ማስፋት እንደሚገባ አንስተዋል።

በተለይም የቱሪዝም ዘርፉን ለማጠናከር፣ ሀገርና ህዝብንም ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላም ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በመገንዘብ ሁሉም የአካባቢውን ደህንነት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።

የጃናሞራ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቄስ መሳፍንት አማረ የአካባቢው ነዋሪዎች ከመንግስት ጎን በመቆም ለሰላምና ደህንነት መጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤትም ከህብረተሰቡ ጋር በመነጋገር እንስሳትን ጨምሮ ለፓርኩ ደህንነት ስጋት ከሚሆኑ ማናቸውም ነገሮች እንዲጠበቅ እየተደረገ ነው ብለዋል።

አካባቢው የተረጋጋና ሰላሙ የተጠበቀ በመሆኑ ጎብኚዎች ይህንን ድንቅ መስህብ እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም