የዓድዋ ድልን ስናከብር የኢትዮጵያን ታሪክና የህዝቦችን የጋራ እሴት በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም መስፈን በመትጋት ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድልን ስናከብር የኢትዮጵያን ታሪክና የህዝቦችን የጋራ እሴት በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም መስፈን በመትጋት ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ
ደብረ ብርሀን፤የካቲት 15/2016 (ኢዜአ)፡- የዓድዋ ድልን ስናከብር የኢትዮጵያን ታሪክና የህዝቦችን የጋራ እሴት በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም መስፈን በመትጋት ሊሆን እንደሚገባ በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የጥንታዊት ኢትዮጵያ አባት አርበኞች ማህበር አስታወቀ።
የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ተክለስላሴ ከበደ ለኢዜአ እንደገለፁት ''የዓድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ነው'' ብለዋል።
ዓድዋን ስንዘክር የጋራ እሴቶችን በማጠናከር፣ መተባበርንና አንድነትን በማጎልበት ዘላቂ ሰላም ማስፈን በሚቻልበት ጉዳይ ላይ በማተኮር መሆን እንዳላበት ገልፀዋል።
ለዚህም ለመላው የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት የሆነውን የዓድዋ ድልን በአግባቡ በመመርመር ምክንያታዊ አስተሳሰብና አመለካከትን መያዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሊቀ መንበሩ አክለው በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ አዲሱ ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ መነሻ በማድረግ በጥናትና ምርመር በመታገዝ ለሀገሩ እድገት እንዲተጋ በአደራ የተሰጠ ቅርስ ነው ብለዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ደረጃ 128 ኛውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ታሪካዊ ዳራውን ጠብቆ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገም መሆኑን አስታውቀዋል ።
ከዓድዋ ድል በመማር ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን ለማስቀጠል መትጋት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ላቀች ንጉሴ ናቸው።
የ128ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በደብረ ብርሀን ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ መሆኑን ጠቅሰው የበዓሉ ማጠናቀቂያ በልዩ ድምቀት ይከበራል ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ ሊቀ መዘምራን ሰይፈ ጥላሁን በበኩላቸው የዓድዋ ድል መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድነትና በጽናት ታግለው ጠላትን በማሸነፍ ያስመዘገቡት ውጤት ነው ብለዋል።
በዓድዋ ድል አባቶቻችን ምርኮኞችን በመንከባከብና ቁስለኞችን አክሞ በማዳን የሰብዓዊነት ጥግ የሆነውን እሴታቸውን ለዓለም ህዝብ ያስተዋወቁበት ጭምር እንደሆነም ተናግረዋል።
ከአባቶቻችን ታሪክ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ለሀገር በጋራ መቆምንና ሌሎች ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በመማር ለሀገር እድገት ተግቶ መስራት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
አባቶቻችን በዚያን ዘመን በሀገር ፍቅር ወድቀው የሀገርን ዳር ድንበር አስከብረዋል ያለው ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት ቢኒያም ደመላሽ ነው።
አሁን ላይ የአባቶቻችንን አኩሪ ታሪክ ለመጪው ትውልድ በማስተላለፍ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም መስራት አለበት ብለዋል።
ወጣቱ ትውድል ከአባቶቹ የወረሰውን አኩሪ ታሪክ ለማስቀጠል የውስጥ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከዓድዋ መማር አለብን ሲልም ተናግረዋል።