የአክሱም ዓጼ ዮሐንስ 4ኛ አየር ማረፍያ ዳግም ግንባታ የከተማዋን ቱሪዝም ያነቃቃል - ኢዜአ አማርኛ
የአክሱም ዓጼ ዮሐንስ 4ኛ አየር ማረፍያ ዳግም ግንባታ የከተማዋን ቱሪዝም ያነቃቃል
አክሱም ፤ የካቲት 15/2016 (ኢዜአ)፦ የአክሱም ዓጼ ዮሐንስ 4ኛ አየር ማረፍያ ዳግም ግንባታ መጀመሩ የተቀዛቀዘውን የከተማውን ቱሪዝም በማነቃቃት ለነዋሪው የስራ እድል እንደሚፈጥር ተገለፀ።
በአክሱም በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ነዋሪዎች በበኩላቸው የአየር መንገዱ ዳግም ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ መንግስት አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያቸው በትግራይ ክልል የሚገኙ አየር መንገዶች ከግማሽ ቢልዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የጥገናና ዳግም ግንባታ እየተከናወኑ መሆኑን መጥቀሳቸው ይታወሳል።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ የአክሱም ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የውጭና አገር ውስጥ ጎብኚዎች አስተባባሪ አቶ ኪዱ ተጠመቀ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የአክሱም ከተማ ህዝብ ኑሮው ከቱሪዝም ጋር የተያያዘ ነው።
በተለይም ለቱሪስቶች የሚሆኑ ዕቃዎች፣ የአገልግሎት ሽያጭ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ተደርገው በዓመት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ይገኝ እንደነበር ለአብነት አንስተዋል።
በዚህም ህዝቡ ከልማቱ እንዲጠቀምና ያገኝ የነበረውን ገቢ እንዲያገኝ የአየር ማረፊያው ግንባታ እንዲፋጠን ጊዜያዊ አስተዳደሩና ጽህፈት ቤቱ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ድጋፍ እንደሚያደርጉም አክለዋል።
የሳብያን ኢንተርናሽናል ሆቴል ዋና ሥራ ስኪያጅ አቶ ጌታቸው አብርሃ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የአክሱም ዓፄ ዮሐንስ 4ኛ አየር መንገድ ዳግም ግንባታ ተደርጎለት አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት ይፈጥራል።
የፌዴራል መንግስት እያደረገ ካለው ስራ በተጓዳኝ ጥገናው በወቅቱ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲጀምር የአክሱም ነዋሪዎች የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በአስጎብኚ ስራ የተሰማራው የአክሱም ከተማ ነዋሪ ወጣት እዝጊ ንኣምን በርኸም ለኢዜአ እንደገለፀው፤ የአክሱም ከተማ ነዋሪ ኑሮ ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር የተቆራኘ ነው።
ነዋሪው በአስጎብኚ ድርጅቶች በኩል በስጦታ ዕቃዎች፣ በጌጣ ጌጥና ቅርፃ ቅርፅ ስራና ሽያጭ እንዲሁም በባህላዊ የዕደ ጥበብ ውጤቶችና ሌሎች ሽያጭ የሚተዳደር መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ማረፊያው ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ከተጠናቀቀ በዘርፉ ለተሰማሩ የከተማው ነዋሪዎች በርካታ የስራ እድል እንደሚፈጥርላቸውም ተናግረዋል።
የአክሱም አስጎብኝዎች ማህበር ሃላፊ ወጣት መርሃዊ ተስፋይ በበኩሉ፤ የአክሱም ዓጼ ዮሓንስ 4ኛ አየር ማረፊያ አገልግሎት መስጠት በማቋረጡ ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተቀዛቅዞ መቆየቱን ተናግሯል።
አሁን ግንባታው በመጀመሩ የከተማው ነዋሪ ተስፋ ሰንቋል ብለዋል።
የአክሱም ዓፄ ዮሐንስ 4ኛ አየር ማረፍያ ዳግም ግንባታ በ290 ሚሊዮን ብር መጀመሩ ይታወቃል።