ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ተሞክሮዎችን ከመለዋወጥ ባለፈ የእርስ በእርስ ግንኙነታችንን እንድናጠናክር ረድቶናል---ተሳታፊዎች

ሶዶ፤ የካቲት 15/2016(ኢዜአ):- 9ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም መልካም ተሞክሮዎችን ከመለዋወጥ ባለፈ እርስ በእርስ ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር አስችሎናል ሲሉ የፎረሙ ተሳታፊዎች ገለጹ።

9ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም "የዘመኑ ከተሞች ለኢትዮጵያ ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል በወላይታ ሶዶ ከተማ ተከብሯል ይገኛል።

ከፎረሙ ተሳታፊዎች መካከል የአዳማ ከተማ ነዋሪ አቶ አንዷለም ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከተለያዩ ክልል ህዝቦች ጋር ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለመፍጠር አግዟቸዋል።

እርስ በርስ በመተባበር፣ በመረዳዳትና በመደመር የአገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማፋጠን ምቹ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት።

ፎረሙ የአዳማ ከተማ ገጽታን ለሌሎች እህት ከተሞች ለማስተዋወቅና የሌሎችንም ልምድ ለመቅሰም እድል መፍጠሩንም አቶ አንዷለም ተናግረዋል።

በፎረሙ ቆይታቸው ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች፣ ተሞክሮዎች፣ የኢንቨስትመንት ፀጋዎች፣ የቱሪዝም ሀብቶች እንዲሁም ታሪካዊና ባህላዊ ትውፊቶችን ከተለያዩ ከተሞች ለመጡ ተሳታፊዎች ማስተዋወቅ እንደቻሉም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የደሴ ከተማ ነዋሪና የፎረሙ ተሳታፊ አቶ ብርሃኑ ገበየሁ በበኩላቸው፣  ከተሞች ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት በመስጠት ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ፎረሙ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

"በፎረሙ ልምድ የተለዋወጥንበት እና የንግድ ሰንሰለት የፈጠርንበት ከመሆኑ በላይ መከባበር፣ መቻቻልና አንድነትን በማጠናከር የጋራ እሴቶቻችንን ያንጸባረቅንበት ነው" ብለዋል።

ፎረሙ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ያጠናከረ በመሆኑ ለአገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አስረድተዋል።

"ፎረሙ በኢትዮጵያ ከተሞች መካከል በፈጠራ የታገዘ ጤናማ ፉክክር እንዲጎለብት በማድረግ የህዝቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት እንዲረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ አለው" ያሉት ደግሞ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቦዲቲ ከተማ የመጡት አቶ ታረቀኝ መንግስቱ ናቸው።

"ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ከማጠናከር ውጭ አማራጭ የለውም" ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ፎረሙ የአብሮነትና የትብብር መንፈስ ከማጎልበት አንጻር አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በከተሞች መካከል የውድድርና የፉክክር መንፈስ እንዲጎለብት በማድረግ የከተሞችን የልማት ጉዞ  ለማፋጠን መነሳሳት መፍጠሩንም ተናግረዋል።

በጠቅላላው ከ150 በላይ ከተሞች የተሳተፉበት 9ኛው የከተሞች ፎረም ትናንት የተጠናቀቀ ሲሆን  ቀጣዩን 10ኛው የከተሞች ፎረም ሰመራ ከተማ እንደምታዘጋጅ ታውቋል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም