ወጣቱ ትውልድ ሰላምን በማስፈንና ልማትን በማረጋገጥ ታሪክ ሰሪ ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ትውልድ ሰላምን በማስፈንና ልማትን በማረጋገጥ ታሪክ ሰሪ ሊሆን ይገባል
ደሴ፤የካቲት 15/2016 (ኢዜአ)፡-"ቀደምት አባቶቻችን አንድነታቸውን ጠብቀው ሀገራቸውን ከወራሪ ጠላት በመጠበቅ ታሪክ እንደሰሩ ሁሉ የአሁኑ ትውልድ ሰላምን በማስፈንና ልማትን በማጠናከር ታሪክ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የደቡብ ወሎ ዞን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጽህፈት ቤት አባላት አስገነዘቡ፡
የጽህፈት ቤቱ ተወካይ ፀሐፊ ተተኪ አርበኛ ማሞ አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት አባቶቻችን አንድነታቸውንና ሰላማቸውን ጠብቀው ለውጭ ጠላት ሳይንበረከኩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስጠብቀዋል፡፡
ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ ተገንዝቦ፣ አክብሮና የጀግንነት ወኔን ተላብሶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስቀጠል የራሱን ታሪክ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ ውጭ መከፋፈልና መጠላለፍ ሀገሪቱን ለአደጋ ከማጋለጥ ያለፈ ለውጥና እድገት አያመጣም ሲሉ ገልጸዋል።
የማህበሩ አባል ተተኪ አርበኛ ሀምሳ አለቃ ባለሟል መለሰ በበኩላቸው ትውልዱ ለሀገሩ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ቀደምት አባቶቻችን አንድነታቸውን ጠብቀው ሀገራቸውን ከወራሪ ጠላት በመጠበቅ ታሪክ እንደሰሩ ሁሉ የአሁኑ ትውልድ ሰላምን በማስፈንና ልማትን በማጠናከር ታሪክ ሰሪ ሊሆን ይገባል ሲሉ አክለዋል ።
ለሀገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት በተከፈለ መስዋእትነት የሴቶች ድርሻ የላቀ እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ ተተኪ አርበኛ መሰረት አለነ ናቸው።
ጀግኖች እናቶች ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ከከፈሉት መስዋትነት ተምረን ሰላም፣ አንድነትና እድገትን በማስቀጠል የራሳችንን ታሪክ ልንሰራ ይገባል'' ብለዋል።
አኩሪ ታሪኮችን በመጠበቅ አብሮነት፣ ሀገር ወዳድነትና ኢትዮጵያዊነትን ማሳዳግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ተተኪ አርበኛ ሀምሳ አለቃ አለማየሁ አበበ በበኩላቸው ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ ድል ተምሮ አንድነቱን ጠብቆ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጋራ ሊያስጠብቅ ይገባል ብለዋል ።
የቀደሙ አባቶቻችን አንድነታቸውን ጠብቀው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቆ የመጣውን የውጭ ወራሪ ኃይልን ድል ነስተው የሀገራቸውን ዳር ድንበር ከወራሪ ኃይል መታደጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
የአድዋ ድል የመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነት፣ የድልና የአሸናፊነት ምልክትና ኩራት መሆኑን ጠቁመው ሁላችንም አንድነታችንን ጠብቀን የራሳችንን ታሪክ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡