የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና መቀመጫ ወደ ኢትዮጵያ ሊዘዋወር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና መቀመጫ ወደ ኢትዮጵያ ሊዘዋወር ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2016 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና መቀመጫ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚዘዋወር የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር(አይባ) አስታወቀ።
ማህበሩ የኢትዮጵያን የቦክስ ስፖርት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።
የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ሕዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብስባ አቶ እያሱ ወሰንን የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡ ይታወቃል።
በኮንፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ፕሬዝዳንቱ የተወከለበት አገር የተቋሙ ዋና መቀመጫ ይሆናል።
የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር(አይባ) ፕሬዝዳንት ኡማር ክሬምሌቭ የፌዴሬሽኑ ዋና መቀመጫ እ.አ.አ በ2024 ከካሜሮን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚዘዋወር ለኢዜአ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ እያሱ ወሰን ለአህጉሪቷ የቦክስ ስፖርት እድገት በንቃት እየሰሩ አንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን እ.አ.አ በሕዳር ወር 2023 በአዲስ አበባ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ዓለም አቀፍ የቦክስ ማዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መጣሉን አስታውሰዋል።
ማዕከሉ ትምህርትና ስልጠናን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።
የቦክስ ማዕከሉን ለመገንባት ከአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመሆን የፕሮጀክት ዝግጅት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ግንባታው እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያና የአፍሪካ የቦክስ ልማትን የተመለከቱ ውይይቶችን ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር የኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
ማህበሩ ለአፍሪካ አገራት የቦክስ ስፖርት እድገት የፋይናንስና የአቅም ግንባታ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝም ነው ክሬምሌቭ የገለጹት።
እ.አ.አ በ2024 በደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንትና የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ስም የቦክስ ውድድር በደርባን ከተማ እንደሚያካሂድና በውድድሩ ላይ በርካታ የአፍሪካ አገራት እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።
ማህበሩ ለተወዳዳሪ አገራት የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደሚያዘጋጅም ጠቁመዋል።
የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር(አይባ) እ.አ.አ በ1945 የተቋቋመ ሲሆን ዋና መቀመጫው በስዊዘርላንድ ሉዛን ነው።
ማህበሩ በስሩ ከአምስት አህጉራዊ ኮንፌዴሬሽኖች የተወጣጡ የ194 አገራትን የቦክስ ፌዴሬሽኖች ይዟል።