ቀጥታ፡

ከአድዋ ድል አሸናፊነትን በመላበስ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ እንተጋለን - የደሴና የባህርዳር ወጣቶች

ደሴ/ባህርዳር  ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፦ ከአድዋ ድል  ጀግንነትና አሸናፊነትን በመላበስ  ለዘላቂ ሰላምና ልማት መስፈን  በትጋት እንሰራለን ሲሉ የደሴና የባህርዳር ከተሞች ወጣቶች ገለጹ።

“አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ “ በሚል መሪ ሃሳብ  በደሴና በባህር ዳር ከተሞች ዛሬ የወጣቶች የውይይት መድረክ ተካሄዷል።

በደሴ ከተማ በተካሄደው መድረክ የተሳተፈችው ወጣት ማዕዛ ተስፋዬ እንዳለችው፤ የአድዋ ድል ጠላትን በማሸነፍ ትውልዱ ቀና እንዲልና የአሸናፊነትን መንፈስ እንዲላበስ ያደረገ ነው።

የአድዋ ድል የቀደሙ አባቶች የድል ታሪክ ቢሆንም ከድሉ ጀግንነትንና አሸናፊነትን በመላበስ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ልማት እንዲረጋገጥ ሚናችን እንወጣለን ብላለች።

ሌላው ወጣት አብዲ አሊ በበኩሉ የአድዋ ድል የሁሉም ጥቁር ህዝቦች ኩራት በመሆኑ ለእኛ ለወጣቶች ትልቅ ትምህርት ነው ብሏል።

የአባቶቻችንን የአብሮነትና የጀግንነት ወኔ ተላብሰንና ሰላማችንን ጠብቀን ኢትዮጵያን በጋራ እናስቀጥላለን ብሏል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሰይድ አራጋው በበኩላቸው" ወጣቱ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊያስከብር ይገባል" ብለዋል።

የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝቦች  የነጻነት አርማና ኩራት መሆኑን በመረዳት ወጣቱ በልማትና ሰላምን በማስከበር ግንባር ቀደም ሆኖ ታሪክ ሰሪ ሊሆን ይገባል ሲሉም አክለዋል።

በተመሳሳይ “የአድዋ ድል ታሪክ ጀግንነት ብቻ ሳይሆን መሪና ተመሪ ተግባብተው የሰሩበትና ግብረ ገብነትም ጎልቶ የታየበት ነው'' ያለው ደግሞ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት ያየህ ጨቡድ ነው።

እኛ ወጣቶች የአድዋን የድል በዓል ከመዘከርና ከማወቅ ባለፈ ለድሉ ውጤት ያበቁ የኢትዮጵያ እሴቶችን በመተግበር ልንተባበር ይገባል ብሏል።

የአድዋ ድል በዓል የአይቻልምን አስተሳሰብ መስበር የቻለና የነጮችን የበላይነት አስተሳሰብ መልክ ያስያዘ መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ወጣት ክቤ የኋላ ናት።

ከአድዋ የድል ታሪክ በመማር ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የበኩሏን ሚና ለመወጣት መዘጋጀቷን ገልፃለች።

የአድዋ ድል ጀግኖች ኢትዮጵያዊን በጽናትና ትብብር ለጥቁር ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ለመላ የዓለም ጭቁን ህዝቦች ያስመዘገቡት የድል ታሪክ መሆኑን የተናገሩት ባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራርና መድረኩን የመሩት አቶ ጊዜው ታከለ ናቸው ።

ወጣቱ የአድዋ ድል በዓልን ከመዘከር ባለፈ ወቅቱ የሚጠብቀውን የልማትና የሰላም አረበኝነት በግንባር ቀደምትነት ሊወጣ እንደሚገባም አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም