የዲጂታል የአድራሻ ሥርዓትን በ73 ትላልቅና መካከለኛ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው

392

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፦ የዲጂታል የአድራሻ ሥርዓትን በ73 ትላልቅና መካከለኛ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ  ገለፁ።

በኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት የለማው የቢሾፍቱ ከተማ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ተግባራዊ ሆኗል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ሚኒስቴሩ አገሪቱን ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሸጋገር የሚያስችሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂና የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ውስጥ የዲጂታል መሠረተ-ልማትና ትስስር  ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ገልፀው፤ የዲጂታል መታወቂያና የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶችም ተጠቃሽ መሆናቸውንም እንዲሁ።

ሌላው የዲጂታል ኢኮኖሚ እውን እንዲሆን ቁልፍ የአስቻይነት ሚና ከሚጫወቱት ውስጥ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት በቀዳሚነት የሚጠቀስ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሥርዓቱ በ73 ትላልቅና መካከለኛ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት የተመረቀው የቢሾፍቱ ከተማ ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓትም የዚህ ዕቅድ አካል መሆኑን ገልጸው፤ ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ ሙሉ በሙሉ ሲተገበር ለእያንዳንዱ ቤትና ሕንፃ እንዲሁም መንገዶች ዲጂታል አድራሻ እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ዲጂታል መሠረተ-ልማቶች አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት።  

በኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ በበኩላቸው፤ ዛሬ የተጀመረው  የቢሾፍቱ ከተማ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ኢንስትቲዩቱ ትኩረት ሰጥቶ ከሚያከናውናቸዉ ለውጥ አምጪ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።


 

ኢንስቲትዩቱ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት በአዳማና በአዲስ አበባ ከተማ ገቢራዊ ለማድረግ ከሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች ጋር ሥምምነት በመፈጸም ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።

የአዳማ ከተማ ሥራው 70 በመቶ መድረሱን ገልፀው፤ የአዲስ አበባ ከተማም  አስተዳደሩ ሥራውን በይፋ መጀመሩን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ሥራውን ወደ ሌሎች የክልል ከተሞች በማስፋት ሁሉንም ትላልቅና መካከለኛ ከተሞችን ለማዳረስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው፤ ሥርዓቱ  አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የተገልጋዮችን መስተጋብር ምቹ የሚያደርግ ነው ብለዋል።


 

ከተማ አስተዳደሩ በዲጂታል የጀመራቸውን አገልግሎቶች ለማቀላጠፍ እንደሚያስችል ገልፀው፤ ሥርዓቱ ተግባራዊ እንዲሆን ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም