በቀጣይ ቀናት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣይ ቀናት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፦በቀጣይ ስምንት ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋፅዖ ሊያደርጉ የሚችሉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአንጻራዊ ሁኔታ እንደሚጠናከሩ የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ በሚቀጥሉት ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋፅዖ ሊያደርጉ የሚችሉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአንጻራዊ ሁኔታ እንደሚጠናከሩ የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ብሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛው፣ በደቡብ ምዕራብ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆና አጎራባች አካባቢዎች የተሻለ ጥንካሬ ይኖራቸዋል ነው ያለው።
በመሆኑም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በመካከለኛው፣ በሰሜን ምስራቅና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች በአንዳንድ ቦታዎቻቸው ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አኃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአጠቃላይ በሚቀጥሉት ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር፣ ጅማ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ ምዕራብ አርሲና አርሲ ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች እንዲሁም የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን፤ በጥቂት ሥፍራዎቻቸው ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተገልጿል።
በተጨማሪም ቡኖ በደሌ፣ ምዕራብ ጉጂና ጥቂት የቦረና ዞን፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ የባህር ዳር ዙሪያ፣ የዋግህምራ ዞኖች፤ ከአፋር ክልል ዞን 1፣ ዞን 4፣ ዞን 3 እና ዞን 5፣ ከትግራይ ክልል የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅ እና የምስራቅ ትግራይ ክልል ዞኖች፣ ከሱማሌ ክልል የሲቲና ጥቂት የፋፈን ዞኖች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ሲል መግለጫው ጠቁሟል።
በሌላ በኩል በጋምቤላ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን ምስራቅና በደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከ35 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ።