በቴሌብር እስካሁን ከ1 ነጥብ 9 ትሪሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ተደርጓል - ኢትዮ ቴሌኮም - ኢዜአ አማርኛ
በቴሌብር እስካሁን ከ1 ነጥብ 9 ትሪሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ተደርጓል - ኢትዮ ቴሌኮም
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፦ ሦስት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው ቴሌብር እስካሁን ከ1 ነጥብ 9 ትሪሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር መደረጉን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ ኩባንያው በውድድር ገበያ ውስጥ ሆኖም ደንበኞችን በማፍራት፣ በገቢና በትርፋማነቱ ውጤታማ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንንም ተከትሎ ኩባንያው በአሁን ሰዓት ዓለም ላይ ካሉ ግዙፍ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው ኩባንያው ባለፉት አምስት ዓመት ከግማሽ ውስጥ 358 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል ነው ያሉት።
ለዚህም ያሉትን ጠንካራ ጎኖች ማስቀጠሉ በተለይም ጥራት ያላቸውን አገልግሎቶች ለደንበኞቹ ለማቅረብ የሚሰራቸው ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንና ወጪ ቆጣቢ አሠራሮች ገቢራዊ መደረጋቸውን በምክንያትነት አስቀምጠዋል።
ሦስት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው አገልግሎቱ እስካሁን ከ1 ነጥብ 9 ትሪሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር እንደተደረገበት ጠቅሰው ይህም ተቋሙ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የራሱን አዎንታዊ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኢትዮጵያ ያላትን ኃብት እንድትጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በተለይም ምርታማነትን ከማሳደግ፣ የምርት ጥራትን ከማስጠበቅ እንዲሁም ወጪ ቆጣቢ አሠራሮችን በመዘርጋት የራሱን አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም በግብርናና ማዕድን ዘርፍ ለሚሰማሩ አካላት የተለያዩ የዲጂታል አሠራሮች ማቅረቡን ጠቁመው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ቴሌብር አገልግሎትን በ2013 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
አገልግሎቱ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የትስስር መንገዶች ገንዘብ ለመላክ፣ ለመቀበልና ለዕቃ ግዥ አገልግሎቶች ይውላል።
በተጨማሪም የትምህርት ቤት፣ የውኃና ኤሌክትሪክ እንዲሁም በድርጅቱ ለሚቀርቡ አየር ሰዓትና የመሳሰሉ አገልግሎቶች ክፍያን በስልክ ለመፈጸም ያስችላል።