ቀጥታ፡

የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችላቸው የእርስ በእርስ ትብብር ሊያጠናክሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016 (ኢዜአ)፦ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ጥራት ለማረጋገጥ የሚያስችላቸውን የእርስ በእርስ ትብብር ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተጠየቀ።  

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎትን ለማበረታታትና የጥራትን ጽንስ ኃሳብ ለማስረጽ የተቋቋመ ድርጅት ነው። 

ድርጅቱ ዓለም አቀፍ የጥራት መለኪያ መስፈርቶችን መሠረት አድርጎ በማወዳደር በጥራት የላቁትን በአገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እየሰጠ ይገኛል።    

ድርጅቱ በ10ኛው ዙር በሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድር ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ድርጅቶች የአሰራር ሥርዓታቸውን፣ ልምድና ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉበትን መድረክ ዛሬ አካሄዷል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ፤ ሣሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) መድረኩ በውድድሩ ተሳትፈው ለሽልማት ያልበቁና በውድድሩ ያልተካፈሉ ድርጅቶች በጥራት የተሻለ አፈጻጸም ካሳዩ ድርጅቶች ልምድና ተሞክሮን የሚወስዱበት ነው።  


 

በዓለም ገበያ ጠንክሮ የተወዳደረ የሚያሸንፍበት፣ በጥራትና በዋጋ ገበያውን የሚቆጣጠሩበት መሆኑን ጠቁመው የአገር ውስጥ ድርጅቶች ይህንን ከግምት ያስገባ ሥራ ለመሥራት ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ነው የገለጹት። 

የአገር ውስጥ ድርጅቶች በተለይም ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር ውጤታማ የጥራት ሥራዎችን በመሥራት የአገሪቱን ተወዳዳሪነት ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። 

ሚዛኑን የጠበቀ ትብብርና ፉክክር ካልተካሄደ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናም ሆነ በሌሎች መድረኮች እንደ አገር ተወዳድሮ ለማሸነፍ ፈተና ሊገጥም እንደሚችልም አሳስበዋል።  

መድረኮችን በመፍጠር እንደ ሀገር መማማር ግድ የሆነበት ወቅት መሆኑን አንስተው በገበያው ውድድር ቀድመው የገቡ ልምዳቸውን ለሌሎች እንዲያጋሩ ጠይቀዋል።

በጋራ ማደግና ማትረፍን ግብን ማዕከል ያደረገ ሥራ በመሥራት የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር አቅም መገንባት ያስችላል ሲሉም ተናግረዋል።  

በዛሬው የልህቀት መድረክ የአሠራር ሥርዓታቸውን፣ ልምድና ተሞክሯቸውን ያጋሩት ሃይንከን ኢትዮጵያና የሜድሮክ እህት ኩባንያ የሆነው ሆራይዘን አዲስ ጎማ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም