ቀጥታ፡

በጎ ፈቃደኞች ደም በመለገስ የወገኖቻቸውን ህይወት የማዳኑን ስራ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

አዳማ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፡- በጎ ፈቃደኞች ደም በመለገስ የወገኖቻቸውን ህይወት የማዳኑን ስራ እንዲያጠናክሩ የኢትዮጵያ ደምና ህብረህዋስ ባንክ አገልግሎት ጠየቀ።

ዜጎች ከህልፈተ ህይወት በኋላ የአይን ብሌንን እንደለግሱ  ለማስቻል የተለያዩ ጥረቶችን እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል

ዛሬ በአዳማ ከተማ የኢትዮጵያ ደምና ህብረህዋስ ባንክ አገልግሎት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ በአይን ብሌን እና የደም ልገሳ ላይ የግንዛቤ ማሳደጊያ ውይይት አካሄዷል።

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ከግማሽ ሚሊዬን በላይ ዜጎች ብርሃን ለማየት የአይን ብሌን ልገሳ እየተጠባበቁ ነው።


 

ከህልፈተ ህይወት በኋላ የአይን ብሌንን በመለገስ እይታን መመለስ በሰው ልጅ ዘንድ ትልቁ ስጦታ መሆኑን ዜጎች ሊረዱት ይገባል ብለዋል።

አገልግሎቱም በዚህ በጎ ፈቃድ ስራ ላይ ዜጎች በስፋት እንዲሳተፉ ለማስቻል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ገልጸው የዛሬው የባለድርሻ አካላት መድረክም ለዚህ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ዜጎች ህይወታቸው ካለፈ በኋላ የአይን ብሌናቸውን እንዲለግሱ ግንዛቤ በማሳድግ ስራ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

አያይዘውም በየዓመቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዬን ዩኒት ደም ለመሰብሰብ የታቀደ ቢሆንም እየተሰበሰበ ያለው 400 ሺህ ዩኒት ደም ብቻ መሆኑን አስታውሰዋል።

በዚህ ዙሪያ ያለውን መቀዛቀዝ ለመቅረፍ የደም ልገሳ ንቅናቄ ከየካቲት 1 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ሁነቶች መከናወኑ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ደምና አይን ብሌን ለመለገስ ማህበረሰቡን ለማንቃት እስከ አሁን የተሄደበት ርቀት በቂ አለመሆኑን አንስተዋል።

ማህበረሰቡን በመረጃ ለመድረስ የሚደረገው ጥረት የሀይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላትን ቢያሳትፍ የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ትምህርት ቤቶችና ህዝብ የሚበዛባቸው ሁነቶች ላይ በመገኘት ቋሚ ደም ለጋሾችን ለማበራከት  ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም የማንቂያ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የሚፈለገውን መጠን ማሳካት እንደሚገባም ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም